












ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር አካል የሆነው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ዘመቻ በክልሉ በይፋ አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብሩ ሁለንተናዊ የአከባቢ ጥበቃ እና የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከስድስት ዓመታት በፊት በክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሳብ አመንጭነት ወደ ተግባር የተገባው የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአከባቢ የአየር ፀባይ ሚዛኑን ከማስተካከል ባሻገር በመንግሥቱ ድርጅት የተጣለውን የዘላቂ ልማት ግብ ለማሳካት የጎላ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ በአከባቢ ጥበቃ እውቅና ያሰጠ እንደሆነ ጠቁመዋል።
መርሀግብሩ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ለምግብነት የሚውሉ እንዲሁም ስትራቴጂክ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በሁለተኛው ምዕራፍ የሚተከሉ ችግኞችን ከምግብ ዋስትና፣ ከልማት ትሩፋት እንዲሁም ከከተማ ውበት ጋር በማስተሳሰር ከመትከል ባሻገር ለክብካቤና ጥበቃ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ በክልሉ ከ1.2 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ያስታወቁት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በዚህ ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በደን መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።
በደን ተከላና ጥበቃ የክልሉ ማህበረሰብ ቱባ ባህል እንዳለው ያወሱት አቶ ማስረሻ በአረንጓዴ አሻራ በተሰራው ውጤታማ ስራ የክልሉ የደን ሽፋን በክልሉ ምሥረታ ከነበረበት አሁን ከ2.9 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል።
በክልሉ ዛሬ እየተከናወነ በሚገኘው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀግብር ብናና ፍራፍሬን ጨምሮ ከ18.9 ሚሊዮን በላይ ጥምር ደን እየተተከለ መሆኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ 70 ከመቶ የተከላ ቦታዎቹ በካርታ የተመላከቱ (Gio referred) በመሆኑ ማነኛውም ሰው የችግኝ ይዞታዎችን በሳተላይት ምስል ከየትኛውም የአለም ክፍል በጎግል ኤርዝ መመልከት የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።
ክልላዊ ማስጀመሪያ በተካሄደበት የካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ጎጀብ አካባቢ የክልሉ እና የካፋ ዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአከባቢ ማህበረሰብ በነቂስ በመውጣት ለተከላ በተዘጋጀው 42 ሄክታር ማሳ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች እየተተከለ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
