




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የክልሉን የፖሊስ ሠራዊት አቅም ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።
የሚወስዷቸው ስልጠናዎች ብቁ ፖሊስ ለመሆን እንደሚያስችላቸው በክልሉ የሞዲዮ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ሰልጣኞች ተናግረዋል።
ሞድዮ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ፤ የመጀመሪያ ምልምል ሰልጣኞቹን ተቀብሎ የፅንሰ-ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ የክልሉን የፖሊስ ተቋም ለማዘመን በሁሉም ዘርፎች ብቁ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋምን በመመስረትና በማጠናከር እንዲሁም የሰራዊት አባላትን አቅም በስልጠናዎችና በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ-ግብሮች በማዳበር ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ተቋሙ ለክልሉ ማደግ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማጉላት የሚያስችሉ የተግባር እንቅስቃሴዎች እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በሞዲዮ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም የወታደራዊ ሥልጠና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አስደሳች አደመ በበኩላቸው ፤ በትምህርት ደረጃቸውና በስልጠና አቀባበል አቅማቸው የተሻሉ ሰልጣኞች ተመልምለው ወደ ተቋሙ መግባታቸውን ገልጸዋል።
አሁን በስልጠና ላይ የሚገኙት ምልምል ሰልጣኞች ለክልሉ የመጀመሪያ ምልምል ሰልጣኞች መሆናቸውን የተናገሩት ዋና እንስፔክተር አስደሳች ፤ በሚቀጥሉት ጊዜያት የክልሉን የፖሊስ ሰራዊት አቅም እንደሚያጠናክሩ ነው የተናገሩት።
ዘንድሮ በኢትዮጵያ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚደረግበት ዓመት እንደመሆኑ ይህንን ስራ ለማሳካትና ሌሎችንም ሀገራዊ ተልዕኮዎች በብቃት የመወጣት አቅም ያላቸውን ፖሊሶች ለማፍራት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚገነዘቡና የሀገርን ሉዓላዊት ማስከበር የሚችሉ የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ከሰልጣኞቹ መካከል ያነጋገርናቸው በመልካም ሥነ-ምግባርና በአካላዊ ብቃት ብቁ ሆነው ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችሉ ስልጠናዎች እየተሰጣቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
በሀገራዊ አስተሳሰብ የኢትዮጵያንና የህዝቧን ጥቅሞች ባስቀደመ አስተሳሰብ ተግባሮቻቸውን እንደሚያከናውኑ ነው የተናገሩት ሲል ቦንጋ ኤፍኤም ዘግቧል።
