በክልላችን የደን ሀብት ጠብቆ ያቆየው ማህበረሰብ በተራው ከመጠበቅ ወደ መጠቀም እንዲሸጋገር እየተሰራ ነው

Spread the love

ሪፖርታዥ

በክልላችን የደን ሀብት ጠብቆ ያቆየው ማህበረሰብ በተራው ከመጠበቅ ወደ መጠቀም እንዲሸጋገር እየተሰራ ነው:- የክልሉ ደን፣አከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት በተለይ በደን ሀብት ከሚታወቁ  ሀገራት ተርታ ትመደባለች። የማህበረሰቡ አኗኗር ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶና ተንከባክቦ የመኖር ባህሉ ዛሬ ለሚናየው ከባቢ አየር ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የክልላችን አብዛኛው አካባቢ የሚታወቀው በጥቅጥቅ ሀገር በቀል ዛፎች በተሞላው ደኑ ነው፡፡ ይህም ደን ለዘመናት ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ ተጠብቆ  የቆየ ቢሆንም ማህበረሰቡ ከዝህ ተፈጥሮ ሀብት መጠቀም ያለበትን ያህል አልተጠቀመም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትልቁ የማህበረሰቡ ጥቅም የአየር ንብረት ሚዛኑ ተጠብቆለት መቆየት ብሆንም መንግስት ተገቢውን ጥቅም ለማስገኘት አየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው በክልሉ የተፈጥሮ ሚዛን አጠባበቅ ዙሪያ ትኩረት አድርጎ ከሚሰሩት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች መካከል የREDD+ 2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና 2018 ዕቅድ በእስትሪንግ ኮሚቴው መገምገሙ ይታወሳል።

የፕሮጀክቱ ትልቅ ትኩረት በሆነው ክለላ 173 ሺ ሄክታር ደንን ወደ ጥብቅ ደን አሠራር ማምጣታቸውን በሪፖርታቸው የገለፁት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ዬርቾ ብርሀኑ ከዝህ በተጨማሪ 187 ሺ ሄክታር አዲስ ተከላ ማካሄዳቸውን አክለዋል።

ከተተከሉት ውስጥ 396 ሄክታር በሀገር በቀል ዛፎች መሸፈናቸውን የገለፁት አስተባባሪው ለፕሮጀክቱ ዓላማ እና የመንግስት ኢኒሼቲቭ አረንጓዴ አሻራ ግብዓት የሚሆን 32 ማዕከላዊ እና 96 የማህበረሰብ (128) ችግኝ ጣቢያዎች በሙሉ አቅም አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።

በደኖች ዙሪያ ማህበራዊ መሠረታቸውን ላደረጉት ዜጎች ዘርፈ ብዙ የኑሮ ማሻሻያ የሚደረግ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት ለ 77 አሳታፊ ደን አስተዳደር ማህበራት እንድሁም ለ36 ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ማህበራት  ድጋፍ መደረጉም ዶ/ር ዬርቾ ገልፀዋል።

የኑሮ ማሻሻያው ለሴቶች እና ወጣቶች የግዴታ በጀት መድቦ መስራቱ የተገለፀ ሲሆን በዶሮ እርባታ፣በበግ ማሞከት፣ በቡናና እንሰት ምርት፣ በዘረመል ማሻሻያዎችና ሶላር ስርጭት ታክሎበት በአጠቃላይ ለ3ሺ 3 መቶ 39 ማህበረሰብ ክፍሎች የኑሮ ማሻሻያው ተጠቃሚ መሆናቸው አብራርተዋል።

በወቅቱ ያነጋገርናቸው የክልሉ ደን፣አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢንጂነር አስራት ገ/ማርያም እንዳሉት እስካሁን በነበሩ ጊዜያት በደን ዘርፉ  የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ ብዙ ያለመሰራቱን ገልፀው  ክልሉ ራሱን ችሎ ከተደራጀበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ መንግስት በሰጠው ትኩረት መሠረት የተፈጥሮ ሀብቱ እየተጠበቀ ነው ብለው ከዚህም  ዘርፍ ማህበረሰቡ እንዴት ተጠቃሚ ይሁን የሚለው በአጽንኦት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኃላፊው አክለው ከእነዚህ ስራዎች አንዱ እና ዋነኛው ከተለያዩ ሀገራት ረጂ ድርጅቶች ጋር ሀገሪቱ በሚትፈጥረው መግባባትና ስምምነት የሚመጣው ትልቅ ፈንድ ለተፈጥሮ ሀብት ባለቤት አካባቢ አንድም ለጥበቃ ሌላኛው ኑሮአቸውን እዚያ አካባቢ ላደረጉ የማህበረሰባችን ክፍሎች የኑሮ ማሻሻያ ማዋል ነው  ብለው ቋሚ የካርበን ክፊያ እስክጀምር ድረስ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅብን አክለዋል።

በክልሉ ተፈጥሮ ላይ  መሠረት ካደረጉት ድርጅቶች  ውስጥ በተደራሽነቱ ሰፊውን ክፍል የሚይዘው REDD+ ነው ያሉት ኢንጂነር አስራት (ዶ/ር) ክቡር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በሰብሳቢነት የሚመሩት ኢስትሪንግ ኮሚቴ በትኩረት ተግባራትን ገምግሞ በመምራቱ እና የአጋር ድርጅቶችን ተግባራት  ከሀገር በቀል እውቀት ጋር በማቀናጀት በመሠራቱ ክልሉ ሲመሠረት 41 በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን ዛሬ ላይ 43.85 በመቶ የክልላችን ቆዳ ሽፋን በጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን እንዲሸፈን መደረጉን አውስተዋል።

ይህ ማለት ከ43 በመቶ በላይ የክልላችን መሬት ለእርሻ አገልግሎት አይውልም ያሉት ዶክተር ኢንጂነር አስራት  ያንን በደን የተያዘ ቦታ ለማህበረሰቡ ከእርሻ መገኘት ያለበትን ጥቅም ከደኑ ዘርፍ እንዲያገኙ እና ለሌሎች አካባቢ ማበረታቻ መሆን እንዲችል  ልዩ ትርጉም ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ከነዝህ ጥቅሞች አንዱ በቀጥታ ኑሮአቸውን ደን ላይ ያደረጉ (በማገዶ እንጨት መቁረጥ፣በከሰል ማከሰል) ላይ መሠረት አድርገው  የሚኖሩ የማህረሰብ ክፍሎች ከዛ ተላቀው፣ የተፈጥሮ ደን ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ቀንሰው ኑሮአቸው እንዲሻሻል በእነዚህ ረጂ ድርጅቶች የሚደረግ ድጋፍ በቀጥታ ወደ ማህበረደቡ እንዲወርድ የማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

እንደ መንግስት ከጊዜያዊ ድጋፍ ባሻገር የማህበረሰቡን ጥቅም ለማረጋገጥ በክልሉ በተለያዩ እንቨስትመንት የሚሰማሩ ድርጅቶች ከዝህ ከባቢ አየር (Eco system) ያገኙትን ጥቅም ለአከባቢው በአሰራር ስርዓቱ መሠረት መልሰው በሚከፍሉበት  ሁኔታ ላይ  እየሰራ መሆኑን ያወሱት ኃላፊው በህደት በሚንሰራው ተግባራት የካርበን ሽያጭ ክፍያ ስርዓቶችን እናረጋግጣለን ብለዋል።

ረጂ ድርጅቶች አሁን እየሰጡ ያሉ ድጋፍ ሊንደርስ ላሰብነው ግብ መዳረሻ ነው እንጂ መጨረሻ ግብ አይደለም ያሉት ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): ለማህበረሰቡ  እኮኖሚውን የሚደግፍ ሀብት እስኪያመነጭ ድረስ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር መስራት ጥቅሙ  የጎላ እንደሆነ ጠቁመዋል።

REDD+ ለተግባር አፈጻጸም የመጨረሻ ዓመት ላይ ስላለ ከቀድሞዎቹ ዓመታት የተሻለ በጀት መመደቡ የተገለፀ ሲሆን የክልሉ መንግስት የአረንጓዴ አሻራ ማጠናቀቂያ ዓመት ጋር አያይዘው ጊዜ እና የፖለቲካ ትርጉም ሰጥቶ በእስትሪንግ ኮሚቴ አማካኝነት እንደሚመራ አመላክተዋል።

ይህ ድርጅት የእስካሁኑ ተግባራት ተለክተው ወደ ክፊያ ስርዓት ሊሸጋገር ስለሆነ በ2018 በጀት ዓመት 3 ከቡና ገለባ ከሰል ማምረቻ ማሽኖች ዝርጋታን ጨምሮ 194 ሺ ሄክታር የተፈጥሮ ደንን በአሳታፊ ደን አስተዳደር ውስጥ ለመከለል፣ 2 ሺ 9 መቶ 78 ሄክታር አዲስ ተከላ፣ 24 አዲስ ማህበራት ማደራጀትና ለ 149 ማህበራት የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ ለማድረግ መታቀዱን መመልከት ተችሏል ።

የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ቢያበቃ እንኳ በሌላ ሞዳሊቲ ስለሚመለስ መንግስት በየጊዜ ከሚያመነጫቸው ኢኒሼቲቮች ጋር አዋህደን ረጂ ድርጅቶች ያስጀመሩትን ተግባራት ለማህበረሰቡ እናስረክባለን ብለዋል የቢሮ ኃላፊው።

ክልላችን ጎልቶ የሚታወቅበት ይህ እምቅ ሀብት የሚጨበጥ ፋይናንስ እስክያመነጭ ድረስ ሁሉም ባለድርሻ ተግቶ እንዲሰራ ያሳሰቡት ኢንጂነር አስራት(ዶ/ር): የካርበን ክፊያ እና የኢኮ ሲስተም ክፊያ እስክረጋጥ እንድሁም የደን ሽፋናችን በፌደራል መንግስት ታሳቢ ተደርገው የበጀት ቀመር አካል እንዲሆን በትጋት እንሰራልን ብለዋል።

በመጨረሻም እነዚህ ድርጅቶች በእድሜ  የተወሰኑና የሚያቆሙ ስለሆነ እርዳታ ቢኖርም ባይኖርም ማህበረሰባችን ከቀደምት አባቶች የወረሰውን ዕንቁ ፀጋ በመጠበቅና በመንከባከብ  የአየር ንብረት ሚዛኑ የተጠበቀለት አካባቢን ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያሸጋግር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *