


የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በአውሮፓውያኑ የ2025 አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ወራቶች በኢትዮጵያን እና ሶማሊያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸው ተገልጿል፡፡
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አደራዳሪነት ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ የታቀደ ነው ተብሏል፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ ከቱርክ ወጣቶች ጋር ቆይታ የነበራቸው ፕሬዝዳንቱ፤ የአንካራው ስምምነት 7 ሰዓታትን የፈጀ እንደነበር በመግለፅ በሁለቱ ሀገራት ትብብር ከስምምነት መደረሱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በመጪዎቹ የጥር እና የካቲት ወራት ወደ ሁለቱ ሀገራት እንደሚያቀኑ መናገራቸውን ቲአርቲ ዎርልድ ዘግቧል፡፡
በንግግራቸው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የበለጠ የቦታ እና የህዝብ ቁጥር ቢኖራትም የባህር በር የሌላት መሆኑ ከባድ እንደሆነ ገልፀው፤ ይህን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ያስከተሏቸውን ውጥረቶች ለማርገብ ቱርክ የማደራደር ስራ መስራቷን አመልክተዋል፡፡
ለስምምነቱ ውጤታማነትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ያላቸው የጠበቀ ግንኙነት ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ነው ፕሬዚዳንቱ የገለፁት፡፡
ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ቱርክ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላት ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቅሰዋል፡፡
በስምምነቱ ለዓለም ህዝብ ለአፍሪካ ቆንጆ ግዜ መሆኑን አሳውቀናል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ቅን ስንሆን እና ሀሳባችን መልካም ሲሆን ሁሉም ነገር ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
