
የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ጤናማና ፍትኃዊ እንዲሁም በሕግና ሥርዓት የሚመራ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴን ለማሣለጥ የተዘጋጀ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ ምንጬ ያልታወቀ ኃብት ማስመለስ፣ ማገድና መያዝን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የዋሉት የሕግ ማዕቀፎች ወጥነት የሌላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ያሉትን የሕግ-ማዕቀፎች ወጥነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ሲባል ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ምንጬ ያልታወቀ ኃብት ለማስመለስ የነበረው የሕግ ማዕቀፍ ከመንግሥት ሰራተኞችና ከህዝባዊ ሰራተኞች ውጪ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ከግምት ያላስገባ መሆኑን ጠቁመው ረቂቅ አዋጁ ይህንን ይቀርፋል ብለዋል።
ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚጠበቅባትን ዓለም አቀፍ ግዴታ ለመወጣትና ውጤታማ ትብብር ለመፍጠር በማለም መዘጋጀቱንም ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።
ረቂቅ አዋጁ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመቀመር በዘርፉ በቂ እውቀትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች አስፈላጊው ጥናት ተደርጎበት መዘጋጀቱን ገልፀው አሁን ላይ ረቂቁ በኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየታየ በመሆኑ በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች ለማሻሻል ክፍት መሆኑንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በአዋጁ ክፍል ወደ ኋላ 10 ዓመታት መሄድና ጉዳዮችን መመልከቱ ፤ ወደ ኋላ ተኪዶ የወንጀል ተጠያቂነት እንዳይኖር በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 22 የተደነገገውን የሚተላላፍ አይደለም ብለዋል።
ይልቁንም በረቂቅ አዋጁ የተመላከተው የፍትሐብሔር ኃላፊነት እንጂ የወንጀል ኃላፊነት አለመሆኑን ገልፀው ይህም ዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ ከግምት ያስገባ መሆኑን ጠቁመዋል።
በረቂቅ አዋጁ በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ የኃብት መውረስ (Non-conviction based forfeiture) ድንጋጌ በልዩ ሁኔታ የገባው ምንጩ ያልታወቀ ኃብት ሆኖ በተለያዩ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ያልተቋጩ ጉዳዮችን ዕልባት ለመስጠት ነው ብለዋል።
የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት መነሻን 10 ሚሊዮን ወለል ያስቀመጠው የአዋጁን ተፈጻሚነት ለማጥበብ መሆኑንም አስረድተዋል።
ረቂቅ አዋጁ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው የሕዝብ ኃብትን የሚመዘብሩ አካላት ላይ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ 8 ክፍሎችና 57 አንቀጾች እንዳሉትም ተገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
