



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ31 ወርቅ አምራችና 1 ወርቅ አቅራቢ ማህበር ላይ እርምጃ መወሰዱ የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ገልጿል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገ/ማሪያም ሰጠኝ ዕርምጃ የተወሰደባቸዉ ከባለፈው 2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ምንም አይነት ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ያላስገቡና የዕቅዳቸውን ከ10% በታች አፈፃፀም ያሳዩ ማህበራት እና ወርቅ አቅራቢያ መሆናቸዉን ነው አቶ ገ/ማሪያም የጠቆሙት፡፡
እነዚህ እርምጃ የተወሰደባቸው በ31 ባህላዊ ወርቅ አምራችና 1 ወርቅ አቅራቢ ማህበር ሲሆኑ ፍቃደቸው ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ተደርጓልም ብለዋል፡፡
በክልሉ ከወርቅ አምራችና አቅራቢ ማህበራት የሚቀርበውን የወርቅ መጠን በቀጣይ ከፍ ለማድረግ ህገወጥ የወርቅ ምርት ዝውውርና ግብይትን በመቆጣጠር ለብሔራዊ ባንክ ብቻ እንዲያቀርቡ ከክልል ጀምሮ ዞንና ወረዳ ድረስ በተቀናጀ ሁኔታ ህብረተሰቡን በማወያየት ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ወርቅ የሚመረትበት ቦታዎች ተከታታይ ድጋፍ በማድረግ የወርቅ ምርት መጠንን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንና አዳዲስ ወርቅ ለማምረት ፍቃድ የወሰዱ ማህበራት ፈጥነው ወደስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ በሰፊው እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ገ/ማሪያም የገለፁት፡፡
የወርቅ አምራችና አቅራቢዎች በሀገር አቀፍ ደረጀ የተሻሻለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የወርቅ ዋጋ በእጅጉ የጨመረ መሆኑን ተገንዝበው የሚያመርቱትን ወርቅ በህጋዊ መንገድ በብሔራዊ ባንክ ግብይት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በቀጣይ እንደ ክልል የተቀመጠውን ወርቅ የማቅረብ ዕቅድ በማያሳኩ እና ዝቅተኛ አፈፃፀም በሚያሳዩ የወርቅ አምራችና ማህበራት ላይ እርምጀ የመውሰድ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ገ/ ማሪያም በአጽንኦት ገልጸዋል ፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
