




የኢትዮጵያ ቤተመጻሕፍት እና ቤተመዛግብት የተለያዩ መጽሐፍት ለምዕራብ ኦሞ ዞን አስረክቧል።
በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አባተ ካሳው እንደተናገሩት፤ አገልግሎቱ እውቀትን በማከማቸትና ለሚቀጥለው ትውልድ በማስተላለፍ ለ80 ዓመታት መስራቱን ተናግረዋል።
ማንበብ እየፈለጉ መፅሐፍት የማያገኙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን አንስተው፤ አገልግሎቱ በትምህርት፣ በማረሚያ ቤቶችና በህዝብ ቤተመጻሕፍቶች የንባብ ባህልን ለማዳበር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ ላይ የተደረገው የመጽሐፍ ድጋፍ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ወጭ የሚያወጣ ነው ያሉት አቶ አባተ ይህንንም በአግባቡ አገልግሎት ላይ ማዋል እንደሚገባ አመላክቷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ ማርቆስ ቡልቻ፤ ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ይህም እውቀት የሚገኘው ከመጽሐፍ ነው ብለዋል።
የመጽሐፍ ስጦታ የስጦታዎች ሁሉ ትልቅ መሆኑን ያነሱት አቶ ማርቆስ፤ የሰው ልጅ እንዲመራመርና እንዲያውቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።
መፅሐፍ ቋሚ እውቀትን ለመፍጠርና ከትውልድ ወደትውልድ ለማስተላለፍ አጋዥ ሲሆን፤ አገልግሎቱ ይህንን ድጋፍ ለሶስተኛ ጊዜ ማድረጉን ምክትል ሀላፊ ገልጸዋል።
በክልሉ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊስ የማጣቀሻ መጽሐፍ እጥረት መኖሩን አንስተው፤ የዛሬ ድጋፍ ይህንኑ ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ተወካይ አቶ አስማማው ምህረት፤ አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ለክልሉ የመጽሐፍ ድጋፍና የቤተመጽሐፍት ባለሞያዎች ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ ቢሮው ከአጋር አካላት ጋር በመሆን አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬው ድጋፍ በሰባት ወረዳዎችና በሦስቱ ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ 12 ትምህርት ቤቶችና ለአንድ የህዝብ ቤተመጻሕፍት የሚሰራጭ መሆኑን አንስተዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጌታቸው ኬኒ በበኩላቸው፤ መጽሐፍ ለሰው ልጅ ከምንም በላይ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ተጨማሪ ንባብ እንዲያነቡ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መጽሐፍትን ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን መጥቅሳቸዉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።
