የክልሉ ትምህርት ቢሮ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፖርታል በይፋ አስጀመረ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ከኢፌዴሪ ትምህርት ምኒስቴር ጋር በመተባበር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፖርታል በይፋ አስጀመሯል።

በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ አስተዳደር ታርጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተካሄደው ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃግብር የተገኙ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመምህራንና ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ አለሙ ፕሮጀክቱ የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ክህሎት ከማሻሻልም ባሻገር በውጤት መሻሻል ላይ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ባህሩ አክለውም ፖርታሉ በትንሽ ዳታ መጠቀም የሚያስችልና በውስጡ በርካታ የእንግሊዝኛ ቋንቋን በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችል የድምፅና የምስል መረጃዎችን የያዘ እንደሆነም አብራርተዌል።

ተማሪዎች በእጃቸው ያለውን ተንቀሳቃሽ ስማርት ስልኮችን፣ ኮምፕዩተሮችንና ታቦችን በመጠቀም ከፖርታሉ መረጃዎችን መጠቀም እንደሚችሉም ተገልጧል።

የታርጫ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ መኩሪያ ማጆር በበኩላቸው ተማሪዎች ፖርታሉን በአግባቡ በመጠቀም የእንግሊዝኛ ቋንቋ መረጃዎችን በማግኘት ራሳቸውን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የታርጫ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ ጮፎሬ በከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች የመረጃ ፖርታሉን እንዲጠቀሙ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ አብራርተዋል።

በትምህርት ቤቱ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች በእጃቸው ባለው ስልክ ሌሎች ጠቃሚ ያልሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ጊዜያቸውን ከሚያባክኑ ለትምህርታቸው ጠቃሚ የሚሆነው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፖርታልን መጠቀም እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፖርታሉ በክልሉ በሚገኙ በሁሉም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *