ባለፉት 9 ወራት 108.5 ኪሎግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ቀርቧል፦የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ

Spread the love

ክልሉ ለማዕድን ዘርፍ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ማዕድናት አንዱ ወርቅ መሆኑንና ሌላኛው የድንጋይ ከሰል ለሀገሪቱ ትልቅ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙና ከውጭ የሚገባውን በሀገር ውስጥ ምርት በመሸፈን ትልቅ አቅም ያላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ እንደተናገሩት ፤ በክልሉ የወርቅ፣ የድንጋይ ከሰልና ሌሎች ማዕድን ሃብቶች በስፋት መኖሩን አንስተው እነዚህን ማዕድናት በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከውጭ ሀገር የሚገባውን የከሰል ድንጋይ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የድንጋይ ከሰሉ ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሄድ በዚህ ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን እየሰረን ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በክልሉ በርካታ ማዕድናት ባለቤት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገ/ማሪያም በኮንታ፣ በቤንች ሸኮ፣ በዳውሮ እና በሸካ ዞኖች ጂኤምስቶን፣ በግራናይት እና ሌሎችም ማዕድናት ላይ የተጀመሩ ጅምር ስራዎች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

በኮንታ እና በዳውሮ ዞኖች የብረት ማዕድን ክምችት መኖሩ የተረጋገጠ በመሆኑ ከፌዴራል የዚህ ማዕድን ፍቃድ ይዘው የመጡ አካላትን ወደ ስራ የማስገባት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አሁን በዋናነት በወርቅና ድንጋይ ከሰል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የገለጹት፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 105 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ የዕቅዱን 48% ማሳካት መቻሉን ጠቅሰው በቀጣይም የሚደረገውን ቁጥጥርን በማጠናከር ህጋዊ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል።

ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውለው 98 ሺህ ቶን የከሰል ድንጋይ በማቀረብ መቻሉንና በማዕድን ዘርፉ ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በሮያሊት መገኘቱ አቶ ገብረማርያም ጠቅሰዋል።

የታቀደውን ዕቅድ በቀሪዎቹ ወራት ለማሳካት ወርቅ በብዛት የሚመረትባቸው ምዕራብ ኦሞ ዞን የቤሮ ወረዳ በረሃማ የሆኑ 4 ቀበሌዎች 40 ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች አካባቢዎች በቅርቡ ድጋፍና ክትትል ተደርጓል በቀጣይ የወርቅ ምርት ይጨምራል ነው ያሉት፡፡

በዘርፉ የማልማት ፈቃድ የተሰጣቸው 165 የወርቅ አምራች ማህበራት መሆናቸዉን ጠቅሰዉ በዚህ ዉስጥ 58 ማህበራት ወደ ሥራ መግባታቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ አዳዲስ የወርቅ ማዕድን ያለባቸው በማጂ፣ በቤሮና ሱሪ ወረዳዎች አካባቢዎች ላይ ፍቃድ በመስጠት ወደ ስራ የማስገባት ስራ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

በወርቅ ማዕድን ላይ ከዚህ ቀደም የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት የማስቆም ስራ በትብብርና በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በከሰል ድንጋይ ከ20 በላይ ፍቃድ አውጥተው ወደ ስራ የገቡ ቢሆንም አሁን በኮንታ እና በዳውሮ ዞኖች 8 ብቻ ስራ ላይ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኢቲ ማይንግ የከሰል ድንጋይ ማበልጸጊያ ፋብርካ በደውሮ ዞን መተከሉንና በቀን 3600 ቶን ከሰል ድንጋይ እንደሚፈጭ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህ ግብአት የሚያቀርቡ በዳውሮ ዞን ከዚህ በፊት የቅኝት ፍቃድ የወሰዱ 23 ማህበራት እንዲሁም በኮንታ ዞን 8 ማህበራት በአጠቃላይ 31 የከሰል ድንጋይ ፍቃድ ያወጡ ማህበራት የምርመራ ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከሰል ድንጋይ ምርት የሀገር ውስጥ የስምንቶ ዋጋ እንዲረጋጋ በማድረግ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋለውን ማናቆዎች በመፍታት የምርት መጠኑ እንዲጨምር ከፍተኛ ርብርብ የሚደረግ እንደሆነ አቶ ገብረማርያም ሰጠኝ ተናግረዋል፡፡

ማዕድን በሚመረትባቸው አካባቢዎች ጥሩ የሆነ የጸጥታ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ገብረማርያም ከዚህ ቀደም ሲል በወርቅ ምርት ላይ ይስተዋል የነበረውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ በመቆጣጠር የምርትና የገቢ መጠንን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በህጋዊ መንገድ ፍቃድ የተሰጣቸው ወርቅ አቅራቢዎች፣ ባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበራት እና ልዩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በክልሉ መኖራቸውን እነዚህ የሚያገኙትን ወርቅ በታማኝነት ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ አሳስበዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *