በ2016 በጀት ዓመት የተሟላ የግብር ህግ ማስከበር ስራ በቅንጅት ይሰራል

Spread the love
ወ/ሮ ትዕግስት በላይ

ወ/ሮ ትዕግስት በላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብር ህግ ማስከበር ዘርፍ ኃላፊ ማህበረሰቡ ግብይት በምፈፅምበት ወቅት ደረሰኝ በመቀበል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የክልሉን ህዝቦች ያደረ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ነው ክልሉ የተመሰረተው ያሉት ዘርፍ ኃላፊዋ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ደግሞ ክልሉ ከሚያመነጨው ኢኮኖሚ ግብርን አሟጦ መሰብሰብ ሲቻል ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ግብራቸውን በታማኝነት የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ቢኖሩም ተገቢውን ግብር በተገቢው መንገድ የማይከፍሉ፤ ደረሰኝ የሚያበላልጡ ሆን ብለው ግብርን የሚያጭበረብሩ ግብር ከፋዮች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነም ተናግረዋል ።

ወ/ሮ ትዕግስት በላይ ቢሮው ለህዝብ ልማት የሚሆን ፋይናንስ መሰብሰብ በአዋጅ ስልጣን የተሰጠው ገቢዎች ቢሮ በመሆኑ ግብርን በተገቢው መንገድ የማይከፍሉ የሚያጭበረብሩ ህገ-ወጦች ላይ ተገቢውን ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት በላይ ባለፉት ሶስት ወራት በግብር ህግ ማስከበር ዘርፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለው በደረጃ ‹‹ሐ›› የዕለት ገቢ ግመታ ስራ ጋር በተያያዘ በተደረገው የማህደር ምርመራ ስራ ጋር በተያያዘ ችግር በፈጠሩ አካላት ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንና በካፋ ዞን ጨና ወረዳ በተሳሳተ የኮንስትራክሽን ፈቃድ ግንባታ ሲፈፅም የነበረ አካል ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በ10ዓመት እስራት እንዲቀጣና 45ሺህ ብር እንዲከፍል በማድረግ ህግ የማስከበር ስራ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል አኳያ ያለውን ክፍተት ለመቅረፍ ግንዛቤ በማስጨበጥ ስራ በየጊዜው እየተሰራ እንዳለና ደረሰኝ በማይሰጡ ነጋዴዎች ላይ ህግ ያመስከበር በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ስራ እየተሰራ እንዳለ ያብራሩት ወ/ሮ ትዕግስት በላይ ማህበረሰቡ ግብይት በሚፈፅምበት ወቅት ደረሰኝ በመቀበል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ 60 የሚሆኑ የኦፕሬሽን ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ከ32 በላይ ውጤታማ ሲሆኑ ስራው በሁሉም የክልሉ ዞኖች ተጠናክሮ መቀጠሉን ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ አክለው ገልፀዋል ሲል የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዘግቧል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *