በወልደሃኔ – ዱርጊ መንገድ ፕሮጀክት አስፋልት ንጣፍ ለመጀመር የቅድመ-ዝግጅት ሥራ በመከናወን ላይ ነው

Spread the love

የማዕከላዊ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን በሚያገናኘው የወልደሃኔ – ዱርጊ መንገድ ፕሮጀክት አስፋልት ንጣፍ ለመጀመር የቅድመ-ዝግጅት ሥራ በመከናወን ላይ ነው።

የመንገድ ግንባታው በዳውሮ ዞን እና በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በኩል በሁለት አቅጣጫ በመከናወን ላይ ሲኾን፥ አጠቃላይ 41 ኪሎሜትር ይሸፍናል።

አሁን ላይ የሰብቤዝ፣ ቤዝኮርስ እንዲሁም የስትራክቸር ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በጠምባሮ በኩል ያለውን የፕሮጀክት ክፍል በአጭር ጊዜ ውስጥ አስፋልት ለማንጠፍ የሚያስችሉ የጠጠር መፍጨት፣ የአስፓልት ፕላንት ተከላ እና ሌሎች ተያያዥ የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል።

የመንገድ ግንባታውን ሀገር-በቀሎቹ ኤም ሲ ጂ ኮንስትራክሽን ከሜልኮን ኮንስትራክሽን ጋር በጋራ በመኾን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የማማከር እና የቁጥጥር ሥራውን ኒች ኢንፍራስትራክቸር ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ከሁብ ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ ጋር በጥምረት በመሥራት ላይ ይገኛሉ።

የመንገድ ግንባታው ከፌደራል መንግሥት በተመደበ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወጪ ነው በመከናወን ላይ የሚገኘው።

የመንገዱ መገንባት የማኅበረሰቡን የዓመታት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠቱም ባለፈ በመንገድ መሠረተ-ልማት አለመኖር ለዘመናት ተራርቀው የነበሩትን የዳውሮ እና የጠምባሮ ሕዝቦች በቅርበት የሚያገናኝ ነው።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቀ ከዚህ ቀደም ከዳውሮ ተነስቶ በወላይታ ሶዶ በኩል ጠምባሮ ለመድረስ ይወስድ ይነበረውን የ250 ኪ.ሜ አድካሚ እና ጥልፍልፍ ጉዞ በቀጥታ ወደ 62 ኪ.ሜ ያሳጥረዋል።

በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን የዓሣ እንዲሁም የተለያዩ የግብርና እና የመዓድን ውጤቶች በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ያስችላል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ከ400 እስከ 500 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እና የዕውቀት ሽግግር የሚያገኙበትን ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *