



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የነዳጅ ምርት ሥርጭትና አስተዳደር እንዲሁም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
ውይይቱ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ የነዳጅ ምርት ሥርጭትና አስተዳደርን ለማሻሻል እና ወጥነት ያለው የቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው።
በውይይቱ የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትልና ንግድና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምዴ ፋሪስ የነዳጅ ሥርጭትና አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የዳሰሰ ሰነድ አቅርበው የጋራ ምክክር ተካሂዷል።
ውይይቱን የመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ መንግስት በድጎማ የሚያቀርበውን የነዳጅ ምርት ከተመደበለት ዓላማ ውጭ እንዳይጠቀም ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረው ጦርነት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ክፍተት እንዳመጣ የገለፁት አቶ ማስረሻ በላቸዉ፤ እስከ ችግሩ መፍትሄ ድረስ የነዳጅ ምርትን በቁጠባ መጠቀምና ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዚህም በየደረጃው የሚገኙ የሚመለከታቸው ተቋማትና አካላት ተግባሩን በጥብቅ ክትትል መምራትና መከታተል አለባቸው ነው ያሉት።
በክልሉ እያጋጠመ ያለዉን የነዳጅ ሥርጭትና አስተዳደር ችግር መኖሩን ጠቁመው፣በዘላቂነት ችግሩ እንዲቀረፍ በየደረጃው በጠንካራ ግብረሃይል ህገ-ወጥ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መግታት፣ ህገ-ወጥ ምርት ግብይትና ዝውውር መቆጣጠርና መከላከል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በክልሉ የነዳጅ ምርትን በአግባቡ ከማሰራጨትና ከማስተዳደር በተጨማሪ በህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ላይ በየደረጃው ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግም የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ ገልጸዋል።
የቢሮ ኃላፊው፤ የሚቀርበዉን የነዳጅ ምርት ለህዝብ አገልግሎት፣ ለጸጥታ ሥራ፣ ለክልላዊ አንገብጋቢ ልማቶች እና ለሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ ሰጥቶ መጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የውይይቱ ባለድርሻ አካላትም በበኩላቸው የሚቀርበው እና የሚሰራጨው የነዳጅ ምርት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል፣ በቁጠባ እንዲጠቀም እና ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዳይከሰቱ በቁርጠኝነት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፍቅር ከበደ
