

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በኢትዮጵያ ቆይታቸው፥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ፖሊሲዎች እና በኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ክሪስታሊና ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በኢትዮጵያ ስላሉ የንግድ እና ኢኮኖሚ እድሎች አስመልክቶ ሀሳቦችን እንደሚለዋወጡም ገልጿል።
የዋና ዳይሬክተሯ ጉብኝት አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ እና የፖሊሲ ምክክሮችን በማድረግ የማይበገር፣ የጋራ እና ዘላቂነት ያለው ብልጽግና እንደሚመጣ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል።
ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እ.አ.አ በ2019 በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ሚኒስቴሩ በመረጃው አስታውሷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
