በተቀናጀና በተሟላ የግብርና ፓኬጅ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራሁ ነው፦ ኮርፖሬሽኑ

Spread the love

ግብርናውን በተቀናጀና በተሟላ ፓኬጅ ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትን በማሳደግ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለፃ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወ/ማርያም በቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ተገኝተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአስር ዓመቱ መሪ የግብርና እቅድ መነሻ የግብርና ግብዓት አግልግሎት አቅርቦት ተደራሽነት ለማስፋፋት በመላው ሀገሪቱ ዘርፍ ብዙ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ-አፈጻሚ አቶ ክፍሌ የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከልም በደቡብ ምዕራብ ቀጠና ለሚገኙ አከባቢዎች ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ በቦንጋ ከተማ በ743 ሚሊዮን ብር፣ በ2.5 ሄኪታር መሬት ላይ ያስገነባው የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል በውስጡ ባለ አራት ወለል የአስተዳደር ህንጻ፣ በአመት ከ150ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ማዘጋጀት የሚያስችል ዘመናዊ የዘር ማበጠሪያ ማሽን፣ የግብርና ግብዓት ማከማቻ መጋዘኖች፣ የእርሻ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂ ማሳያ እንዲሁም ዘመናዊ የዘር ቁጥጥር ላብራቶሪን ያካተተ መሆኑን ነው አቶ ክፍሌ ያስረዱት።

ኮርፖሬሽኑ አለምአቀፍ የጥራት መመዘኛዎችን ያሟሉ ምርጥ ዘሮችን በማምራት ለሀገር ውስጥና ለአለም ገበያ ለማቅረብ ከማሳ ዝግጅት እስከ ጎተራ የተሟላ የጥራት ቁጥጥርና ክትትል ስርዓት እንዳለው የገለጹት ኃላፊው ማዕከሉ በቀጠናው ምርታማነቱ የተረጋገጠ ዘር ለአርሶና ከፍል አርብቶአደሮች በተመጣጣኝ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

የኮርፖሬሽኑ ማዕከል በዋናነት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ ከፍል ኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች ተደራሽ በመሆን የተሟላ የዘርና ግብርና ግብዓት አቅርቦት፤ የአፈር ማዳበሪያና ፀረ ተባይ ኬሚካል አቅርቦት፤ የእንሳሳት መድኃኒት አቅርቦት፣ የተፈጥሮና ኬሚካል ማዳበሪያ እንዲሁም የእርሻ የሜካናይዜሽን አግልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ነው የገለጹት።

የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የመሬት ዝግጅት እና የምርጥ ዘር አጠቃቀም እንዲሁም የተሟላ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ከማሳለጥ ባሻገር አጠቃላይ የስነ እርሻ ዘዴ ለማሻሻል ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው አቶ ክፈሌ የገለጹት።

ማዕከሉ በቀጠናው በስፋት የሚመረተውን የበቆሎ ምርት በአጭር ጊዜ ከማሳ እስከ ጎተራ የሚሰበሰብ የእርሻ ቴክኖሎጂ በክራይ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርብ የገለጹት አቶ ክፍሌ ይህም የአርሶአደሩን ጊዜና ጉልበት ከቀነሰ ባሻገር የምርት ብክነት በእጅጉ የሚቀንስ አዲስ ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል።

ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በማዕከሉ በሽያጭ ለሚቀርቡ ከቀላል እስከ ውስብስብ የእርሻ ቴክኖሎጂዎች የባለሙያ ስልጠና፣ የመለዋወጫ አቅርቦት እንዲሁም አጠቃላይ የድህረ ሽያጭ የተሟላ አግልግሎት የሚሰጥበት መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ማዕከሉ ከማሳ ዝግጅት እስከ ምርት ብዝዬት በሚያደርገው ረዥም የእሴት ሰንሰለት ሂዴት ለበርካታ የአከባቢው ወጣቶች በቋሚነትና በጊዚያዊነት የሥራ ዕድል የሚፈጠርም መሆኑ ነው የገለጹት።

የመንግሥት የልማት ድርጅት የኾነው ኮርፖሬሽኑ የአፈር ማዳበሪያን በብቸኝነት በሀገሪቱ እያቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት ስራ አስፈፃሚው መንግሥት እንደሀገር ግብርናን ለማዘመን ያቀደውን ተልዕኮ በማሳካት ረገድ ኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

የቦንጋ ማዕከል ግንባታው የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ተመርቆ የተሟላ አግልግሎት መስጠት እንደሚጀመርም ስራ አስፈፃሚው ጨምረው ገልጸዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *