12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ በኦሚያ ቀበሌ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ 3162 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል ።

Spread the love

በምረቃው ስነስርዓት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው እንደገለጹት የኦሚያ ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ በ2011 ዓ/ም ተገንብቶ ለዓመታት ሳይጠናቀቅ በመቆየቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱንና አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ የህዝቡን ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።

በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ ተጀምረው የተቋረጡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ተከታትሎ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ መንግስት ከ270 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ከ400 ሺህ በላይ የክልሉ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሆነም ኢንጂነር በየነ ተናግረዋል ።

የኦሚያ ንጹህ መጠጥ ውሃ የአካባቢውን 3162 ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ኢንጂነር በየነ በላቸው ተናግረዋል ።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተሰሩ ስራዎች የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 43.73 ከመቶ መድረሱንም ኢንጂነር በየነ ተናግረዋል ።

የካፋ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በሰጠው ትኩረት ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃት መቻሉን ተናግረዋል ።

ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የኦሚያ ቀበሌ ንጹህ መጠጥ ውሃ ለረጂም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የጠሎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትርሴ ሻታቸው እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት አካባቢውን ማህበረሰብ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

የኦሚያ ንጹህ መጠጥ ውሃ ከጎሪ ምንጭ የተገነባ ሲሆን የምንጭ ማጠራቀሚያ 2 7 ቦኖ በትምህርት ቤት 2 የእጅ መታጠቢያ እና የጄኔሬተር ቤትና 2.3 ኪሎሜትር የውሃ መስመር ግንባታ ተከናውኗል ብለዋል ።

በምረቃው ስነስርዓት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣የካፋ ዞን አመራሮች፣የጠሎ ወረዳ አመራሮችና የኦሚያ ቀበሌ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *