









የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ የስድስት ወራት አፈጻጸም በቦንጋ ከተማ ተገምግሟል።
በፖለቲካና በአደረጃጀት ዘርፎች እንዲሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ከእቅዱ መነሻ በርካታ ተግባራት መፈጸማቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በግምገማው መድረክ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የውስጠ ፓርቲ አንድነትና ጤንነት በማስጠበቅ ረገድ አመራርና አባሉ ምሳሌ መሆን መቻል እንዳለበት ጠቁመዋል።
አመራሩ በሁሉም ተግባር ውጤታማ በመሆን በብልጽግና ፓርቲ መርህና ዕሳቤ ላይ ተመርኩዞ ተግባራትን በተሻለ መልኩ መፈጸም እንደሚጠበቅበት ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት በፓርቲው መሪነት የተገኘውን የተሻለ አፈጻጸም አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በአብሮነት እሴቶች እርስ በርስ በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ ተግባርን በትጋት ያስፈልጋል ነዉ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ።
ህብረብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን የብልጽግና ህልሞችን ከዳር ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር የአገልጋይነት ስሜት ተላብሶ ተግባራትን በእውቀትና በክህሎት መምራት እንደሚጠበቅበት የጠቆሙት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን አመራሩ ዕድልና ፈተናዎች በተገቢው በመለየት ለህዝብ ተጠቃሚነት መትጋት ይገባል ብለዋል።
በመንግሥት ክንፉ የሚሰሩ ተግባራት በተጨባጭ መኖራቸውን በድጋፋዊ ክትትል የማረጋገጥ፣ በአመራሩ መካከል የሀሳብና የተግባር አንድነት መፍጠር እንዲሁም ክልላዊ አንድነት ማጠናከር የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ነው አቶ ፍቅሬ የገለጹት።
በየጊዜው ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታን በዝርዝር በመገምገም አጀንዳዎች እየተለዩ ለአስፈፃሚው አካላት በማቅረብ በልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በሠላም ግንባታ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን የመፍታት ተግባር መከናወኑ የገለጹት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ በክልሉ ብልጽግናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራት ተከናውኗል ብለዋል።
የአስተሳሰብ ልዕልና በማረጋገጥ ሁለንተናዊ ብልጽግናና ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ ተግባራት ስለመፈጸማቸው የገለጹት አቶ ነጋ፥ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት የተለያዩ የንቅናቄ ፣ የአባልና አመራር አቅም ግንባታ መድረክ በማካሄድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት መፈጠር መቻሉን አብራርተዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር የፓርቲና የመንግሥት ተግባራትን አቀናጅተው ከመምራት አኳያም ውስንነቶች እንዲተስተዋልበት የጠቆሙት አቶ ነጋ በቀጣይ ችግሮችን ፈጥኖ በማረም የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት ፣ ክልላዊ አንድነትን ማስጠበቅ እንዲሁም ችግሮችን በመፍጠንና በመፍጠር ዕሳቤ በውይይትና ንግግር የመፍታት ባህል ማዳበር ይገባል ብለዋል።
ጠንካራ የፓርቲ አሰራርን በየደረጃው መትከል ይገባል ያሉት በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊዉ አቶ በላይ ተሰማ የፓርቲውን አደረጃጀትና ወይይት በማጠናከር ተልዕኮውን መፈጸምና ማስፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአባልና አመራር የሚዲያ ተሳትፎ በማሳደግ የፓርቲውን ዕሳቤ በስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የጠየቁት አስተያየት ሰጪዎች በህዝብ አግልግሎት አሰጣጥ የሚታዩ ጉድለቶችን በዘላቂነት ለማረም ህዝባዊ ውይይቶችን በየደረጃው መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
