በክልሉ ለጤና ልማት ሥራዎች ትኩረት በመስጠት የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን በማረም የማህበረሰቡን ጤና ማስጠበቅ ይገባናል ሲሉ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የ2017 በጀት ዓመት ክልላዊ ማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት” የጤና መድህን አገልግሎት ለጋራ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂደዋል።

በመድረኩ የ2017 በጀት ዓመት የማህበረሰብ ዓቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት የእስካሁን አፈጻጸምና ማቀጣጠያ ንቅናቄ ሰነድ ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በመድረኩ እንደገለጹት፤በክልሉ ለጤና ልማት ሥራዎች ትኩረት በመስጠት የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮችን በማረም የማህበረሰቡን ጤና ማስጠበቅ ይጠበቅብናል።

በተለይም በሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻልና ማዘመን፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር መቅረፍ፣የውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ከህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን መፍታት ቅድሚያ የሚሰጡ ጉዳዮች እንደሆናቸውም ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ጠቁመዋል።

በክልሉ በጤና መድህን አገልግሎት የታየውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ማረም እንዲያስችል ንቅናቄውን ወደታች ማውረድና የጋራ ውይይት መድረኮችን በመፍጠር ረገድ የዞን፣የከተማ አስተዳደር እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጤና መድህን አገልግሎት ለማህበረሰብ ጤና እና ለጤና ዘርፍ ስኬት የሚያስገኘው ጠቀሜታ የጎላ በመሆኑ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፣የደሃ ደሃ ማህበረሰብ ክፍሎችን ልየታ እንዲሁም ሁሉም ጤና ተቋማት የጤና መድህን ህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸም ከነበረበት ደረጃ ከፍ እንዲል አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የጤና አመራሩና ባለሙያው ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም አሳስበዋል ።

በጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻል፣የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ይሰራል ያሉት የቢሮ ኃላፊው፤ የ2017 አዳዲስ አባላት ማፍራት ፣ነባር ዕድሳት፣ ዕዳዎችን መክፈል መዋጮ አሰባሰብ እንዲሁም ሀብት አሰባሰብ ሥራዎች በተያዘው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሁሉም መረባረብ እንደሚገባዉ ኃላፊዉ ተናግረዋል።

የሀብት አሰባሰብና ሌሎች ሥራዎች በትኩረት እንዲመሩ አቅጣጫ ተቀምጦ በቀጣይ 1 ወራት የሚከናወኑ ተግባራት ላይ ርዕሰ መስተዳደሩ ከዞን ዋና አስተዳዳሪዎች ጋር ተፈራርመዉ መድረኩ ተጠናቋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *