




በሚቀጥሉት 3 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ሊተገበሩ በታቀዱ ሥራዎች ዙሪያ በቦንጋ አተማ ውይይት ተደርጓል።
ውይይቱ “ከዕምቅ አቅም ወደሚጨበጥ ሀብት” በሚል መሪ ቃል በክልሉ መንግስት የተዘጋጀ የፖለቲካና የልማት ውይይት ሲሆን ፤ ክልሉ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፉ በርካታ ሀብቶች ባለቤት መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ ያሉ የመልማት አቅሞችን በተገቢው መለየትና መጠቀም፣ ህብረተሰቡን በማስተባበር ልማታዊ ስራዎችን ማጠናከር፣ የአመራሩን እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ማሳደግ የሚያስፈልግ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል።
በሰላምና ፀጥታ፣ በልማት ፣ በመልካም አስተዳደር እና በፖለቲካ ዘርፎች የህብረተሰበቡን ጥያቄዎች ለመመለስ መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ ጉዳይ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ ክልሉ የበርካታ ሀብቶች ባለቤት ነው ብለዋል።
ይህንን ሀብት ለመጠቀም አመራሩና ህዝቡ የተግባር አንድነትን መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።
ባለፉት ጊዜያት በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች የተከናወኑ ተግበራትን በጥራትና በፍጥነት ከመከወን አንጻር የታዩ ክፍተቶች እንዳይደገሙ የጋራ ግንዛቤ መያዙን ተናግረዋል።
በተለይ ክልሉ በሚታወቅባቸው ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ-ቅመምና ማር እንዲሁም የተለያዩ ማዕድናትን በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ወደ ሀብት ለሚደረገው ጉዞ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ክልሉ በእንስሳት ሃብት በእንሰትና ሌሎችም በርካታ ዘርፎች ያለዉን እምቅ ሃብት በአግባቡ ያላሳየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አጣፉ ሃይሌ ናቸዉ።
ከዚህ ቀደም ወጥ ባልሆነ አሰራር ሲሰሩ የነበሩ ተግበራትን በማስተካከል በቀጣይ 3 ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ለዉጦችን ለማስመዝገብ ወደ ተግባር ገብተናል ያሉት አቶ አጥናፉ በተለይ እንደ ሃገር ትልቅ ሃብት የሚያስገኙ የግብርና ምርቶችን አዉጥቶ ለማሳየት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃብታሙ ካፍትን ከዚህ ቀደም በመደበኛ ስራ ሲከወኑ በቆዩና ልዩ ትኩረት ባልተሰጣቸው ጉዳዮች ዙርያ በክልሉ ሃሳብ አመንጪነት ይህ ዉይይት መደረጉ ትልቅ ለውጥ ይዞ የሚመጣ ይሆናል ብለዋል።
ከዚህ በተለየ በቀጣይ 3 አመታት የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር የጸዳ እንዲሆን ክትትል ማድረግ፣ ህገ-ወጥ ንግድን መቆጣጠር፣ ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎች በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ በየደረጃው ቅሬታ የሚፈታበትን አሰራር ማጠናከር የሚያስፈልግ መሆኑ በመድረኩ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።
በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ አስፈጻሚ አካላት፣ የዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ሰል የቦንጋ ኤፍ ኤም 97.4 ዘግቧል።
