



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሚዛን ማዕከል የብልጽግ ህብረት አባላት “ከቃል እስከ ባህል” በሁለተኛው የፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎች የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በሚዛን አማን የውይይት መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ ለውይይት መነሻ ሰነድ የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎችም ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሚዛን ማዕከል የብልጽግና ህብረት አባላት እንደተናገሩት የፓርቲውን ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣዎች ተፈጻሚ ለማድረግ አመራሩና አባላት ግንባር ቀደም በመሆን ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። ለዚህም በአመራሩና በአባላቱ የአመላካከትና የተግባር አንድነት ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ብልጽግና በመጀመሪያው ጉባኤ ጀምሮ በዕቅድ የያዛቸውን በተጨባጭ በመፈፀምና ባህል አድርጎ ከማስቀጠል አንጻር በርካታ አመርቂ ተግባራት ተፈጽመዋል ብለዋል። እንደ ሀገር በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፣ በግብርና በማዕድን ፣ በኢንዱስትሪ እና በቱሪዝም ዘርፉ የመጡ ውጤቶችን ማስቀጠልና ብልጽግና በጽኑ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ይገባል ብለዋል።
በኑሮ ውድነት ፣ በዋጋ ንረት ፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በጤና ፣ በትራንስፖርት ፣ በናፍጣና ቤንዚን እጥረት የሚታዩ ውስንነቶችን ለቅሞ መስራትና መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል። ነጣጣይና ከፋፋይ ትርክቶችን በገዢ ትርክት የመለወጥና አንድነትን ማጽናት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የክልል ሴክተር መስሪያ ቤት ኃላፊዎችም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊና የሚዛን ማዕከል ብልጽግና ህብረት ሰብሳቢ አቶ ጸደቀ ከፍታው መድረኩን ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት ብልጽግና ፓርቲ ከለውጡ ማግስት እንደ ሀገር የገጠመንን ፈተናዎች በጽናትና በጥበብ አልፎ ዛሬ ሀገርን ያስቀጠለ ፓርቲ ነው ብለዋል።
የአባላትና አመራሩ ጠንካራ አቋምና አንድነት ለቀጣይ አቅጣጫዎች ስኬት ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ጸደቀ ሁሉም በተሰማራበት መስክ ተግባራትን በውጤት ማጀብ ይጠበቅበታል ብለዋል። በቀጣይ አቅጣጫዎች ውስጥ የኑሮ ውድነትን መቀነስ ፣ ሰላምን ማጽናት ፣ ግብርናን ማዘመን እንዲሁም ብሔራዊነትን ማጽናትና መሰል ተግባራት ቁልፍ ስራዎች ተደርገው ይሰራሉ ብለዋል።
