




የክልሉ ጤና ቢሮ የ2017 ዓመተ ምህረት ዓመታዊ ሪፖርትና የ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል።
የቢሮውን የ2017 ዓመተ ምህረት ዓመታዊ ሪፖርትና የ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር እንዳለ ሳህሌ በዳይሬክቶሬቱ በርካታ የጤና ማጎልበት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከነዚህም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዋነኛ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር እንዳለ በአሁኑ ሰዓት ከ1 ሺህ 4ዐዐ በላይ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እንደ አዲስ በስልጠና ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ባለሙያዎቹ በዋናነት የማህበረሰብ ተሳትፎ ማሳደግና የሴቶች አደረጃጀትን በማጠናከር የበሽታ መከላከል አቅማችንን ከፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
በእስካሁኑ እንደክልል 85 በመቶ የተደራጁ አደረጃጀቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ያም ሆኖ የተጠናከሩ ባለመሆናቸው የተፈለገወን ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቅሰዋል።
ይህም በመሆኑ እንደክልል በቂ ሞዴል ቀበሌና ወረዳን መፍጠር አለመቻሉን የገለጹት ዶ/ር እንዳለ በዚህም ክልሉ እንደሀገር በ52 በመቶ ሞዴል ወረዳ አፈጻጸም 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም በአጠቃላይ ጤና ኬላዎች ግንባታና ብቁ ባለሙያ ምደባ፣ በቤተሰብ ጤና ቡድን ማደራጀት፣ ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤት ግንባታን ጨምሮ በተላለፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ክልሉ የጀመረውን ጥረት ለማሳካት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በወባ ከ1 ነጥብ 3 ሚልዮን በላይ ሰዎች ታመው ህክምና ማግኘታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር እንዳለ በተለይ ለህክምናው ተደራሽነት የጤና ኬላ ግንባታን ማጠናከር ላይ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
በተለይ ወባን ለመከላከል የሚያስችል አጎበር ለ21 ወረዳዎች፣ የኬሚካል ስርጭት ደግሞ ለ11 ወረዳዎች ተደራሽ የሆነ ሲሆን የሀገሪቱ 20 በመቶ የወባ በሽታ ክትባት ሽፋን ለክልሉ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
