የበጀት ዓመቱ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የዘር ሽፋን ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት ነው – ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

Spread the love

የበጀት ዓመቱ የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የዘር ሽፋን ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩም የግብርና ስራዎች አፈፃፀም በስፋት ውይይት የተደረገበት መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

የ2015/16 የምርት ዘመን ከታቀደው እቅድ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ምርት የተሰበሰበበት መሆኑንም አንስተዋል።

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የላቀ ስኬት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው በዚህም 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኖ 106 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።

በበልግም 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመዝራት ከእቅዱ በላይ ተሳክቷል ብለዋል።

ለግብርና ልማት የግብዓት አቅርቦት ዘንድሮ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አንስተው በተለይም በአፈር ማዳበሪያ ግዥና ስርጭት የተሻለ አፈፃፀም መኖሩን አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት በ930 ሚሊዮን ዶላር የተገዛው 20 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከአምናው የ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገና በዜጎች አኗኗር ላይ እመርታዊ ለውጥ ያመጣ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *