የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ፦ አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን በክልሉ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ፍቅሬ አማን ገለጻ ፦ በ2018 በአንደኛ ሩብ ዓመት በመንግሥት እና ፓርቲ መሪነት በመደበኛ እና በንቅናቄ የሚመሩ አጀንዳዎችን መፈጸም እንዲያስችል ከዕቅድ ዝግጅት አንስቶ በአስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች ዘንድ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ለመፍጠር ሰፊ ተግባራት መከናወናወኑን ተናግረዋል።

መንግሥት እና ፓርቲዉ በየጊዜው የሚያወርዳቸዉና የሚያስቀምጣቸው ግቦችና ተልዕኮችን መፈጸም የሚችል የአመራር ሥርዓት ለመዘርጋት አፈጻጸምን መነሻ ያደረገ የአመራርና አባላት ግምገማና ምዘናዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።

ከግምገማና ምዘናዉ መነሻ ከክልል እስከ ወረዳ መዋቅር ከ435 በላይ አመራሮችን በአዲስ ወደ አመራርነት ማቀላቀል፣ማሸጋሸግ እና ከቦታ ማንሳት መቻሉን የጠቀሱት አቶ ፍቅሬ፤ ተልዕኮን መፈጸም የሚችል አመራርንና አባላትን ለማፍራት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንም እንዲሁ።

ፈጠራን እና ፍጥነትን ማዕከል ባደረገ የሕዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን የማይመልሱ፣ የአፈጻጸም ድክመትና የድስፕሊን ችግር የታየባቸው አመራሮችንና አባላትን በመገምገም ማስተካከያ እና የእርምት እርምጃዎች የተወሰደባቸው ሲሆን ተግባሩ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንደሚከናወንም አንስተዋል።

አፈጻጸሞችን መነሻ በማድረግ የተከናወነው ግምገማና ምዘና ለበጀት ዓመቱ ለላቀ ሥራ የሚያነሳሳ እና መነቃቃትን የፈጠረ ነው ያሉት አቶ ፍቅሬ አማን፤ በፓርቲው መሪነት በፖለቲካና አቅም ግንባታ፣ አደረጃጀት፣ ዴሞክራሲ ባህል ግንባታና በሌሎች ዘርፎች ሰፊ ተግባራት መፈጸማቸውንም አብራርተዋል።

እንደሀገር ብልጽግና ፓርቲ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሦስት ወራት ታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠናቅቀዉ ከማስመረቅ ባሻገር ትላልቅ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አስጀምረዋል ያሉት አቶ ፍቅሬ በክልላችም የፓርቲውን እሳቤ እና ዕቅዶችን በተሳለጠ ማከናወን የሚያስችሉ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ነዉ የገለጹት።

2018 በጀት ዓመት የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ሌሎች ሀገራዊ ድርብርብ ተልዕኮዎች የሚፈጽሙበት ዓመት በመሆኑ ይህንን ታሳብ ያደረጉ ሥራዎችን ለማከናወን በየደረጃው ያሉ ተቋማትና አካላት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።

በፓርቲው መሪነት ከሚተገብሩ በርካታ ኢንሼቲቮች መካከል ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን አንዱ ተግባር መሆኑንም ጠቁመው በክልሉ ያለዉን ጸጋ በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ተረጅነትን ለመቀነስ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል አቶ ፍቅሬ አማን።

አቶ ፍቅሬ አማን ብልጽግና ሰብአዊነትን የሚያስቀድም ሰዉ ተኮር ፓርቲ በመሆኑ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማዎችን በማገዝና መደገፍ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም በመግለጽ ሌማት ትሩፋት እንዲሁም በከተማና ገጠር ኮሪደር ልማት ኢንሼቲቭ ሥራዎች ጥራትና ውጤታማነትን እያረጋገጥን መጓዝ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

ኑሮ ውድነትን ለማቃለል የግብርና ምርታማነት ማሳደግ፣ አላስፈላጊ ኑሮ ውድነት የሚያባብሱ ብልሹ አሠራሮች ላይ እርምጃ መውሰድ እንዲሁም ሰንበትና ምሽት ገበያዎችን ለማስፋፋት ትኩረት ይደረጋል ያሉት አቶ ፍቅሬ፤ የሃገር ውስጥና ውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪቶች ብሎም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይሰራልም ብለዋል።

እንደሀገር ባለፉት ዘመናት የተፈራረቁ ሥርዓቶች ሀገራችንን ከድህነት፣ ከጦርነትና ሀገሪቷ ሀብቷን በነጻነት እንዳትጠቀም ማድረጓንም ጠቅሰዉ ብልጽግና ፓርቲ እነዚህ ስብራቶችን መጠገን የሚያስችሉ እሳቤ፣ ዕቅድና ፕሮግራሞችን ይዘዉ የመጣ በመሆኑ አመራሩና አባሉ ግንባር ቀደም በመሆን ተግባራትን መምራትና ማከናወን ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

እንደአቶ ፍቅሬ አማን ማብራሪያ ፤ ክልሉ ከተመሠረተ ማግስት አንስቶ በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የአመራሩ እና አባሉ ሚና ቀላል የማይባል መሆኑንም ጠቅሰው ህዝቡ ከሚፈልገው ውጤት አኳያ አሁንም በተቀናጀና በተጠናከረ መሥራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

በአንደኛው ሩብ ዓመት የተጀመሩ ተግባራትን በማጠናከር በቀሪ ወራት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ አገልግሎት አሰጣጥ ማሳለጥ፣ ሌብነት እና ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ አመራሩ በአገልጋይነት መንፈስ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አስምረውበታል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመፍታት ተቋማት፣ አስፈጻሚዎችና ፈጻሚዎች በዕቅድ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከዕጅ ንክኪ የጸዳ እንዲሆን በቴክኖሎጂ ማዘመንና በክልሉ መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የማስፋፋት ሥራዎች እንደሚከናወንም አብራርተዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *