

የፀጥታና ደህነት የጋራ ግብረ ሃይሉ የፊታችን የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም የሚከበረው 128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በአል ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማስቻል በወጣው የማስፈፀሚያ እቅድ ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሰላም አዳራሽ ላይ ውይይት አድርጓል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻ ሀላፊ ጀነራል ተስፋዬ አያሌው በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል የሆነው የአድዋ ድል በአል ሲከበር ምንም አይነት ስጋት እንዳያጋጥም የፀጥታ ሀይሉ ዝግጁ መሆኑን ገልፀው የበዓሉ ተሳታፊዎች ፀብን ከሚያነሳሱ እና በዓሉን የማይገልፁ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን ከመፈፀም ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ተገንብቶ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ የዘንድሮውን የአድዋ ድል በአልን ልዩ እንደሚያደርገው አስታውሰው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከብሮ እንዲውል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደተናገሩት ለ128ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በአል የሚያውኩ ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ በመዲናችን ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በማጥናትና በመለየት ችግሩን ለማስወገድና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ።
በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ሀላፊ ምክትል ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ በበኩላቸው የአድዋ ድል በአል መከበርን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት ለመፍጠርና የግል ፍላጎታቸውን ለማንፀባረቅ የሚሞክሩ አካላት በሚያጋጥሙበት ወቅት ለፀጥታ ሃይሉ በመጠቆም ህብረተሰቡና የበዓሉ ተሳታፊዎች የተለመደ ትብብራቸውን ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።
