




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡናና ሻይ፣ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን የ2016 ምርት ዘመን የቡና ምርትና ግብይት ጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ ግበረ-ኃይል የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄደ።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ቡናን በአግባቡ በማምረት ለአለም ገበያ ማቅረብ የሀገሪቱን ጥቅም ማስከበር በመሆኑ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ዘርፉን ትኩረት ሰጥተው መምራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በክልሉ የቡና ልማትን ማስፋትና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ ፓኬጆችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የግብይት ሂደቱን ጤናማ በማድረግ ከህገወጦች መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአምራች አርሶአደሩን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርቶችን በጥራትና በብዛት ማምረት ተገቢ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ማስረሻ በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን ተቀናጅቶ በመስራት መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህም በክልሉ የቡና ምርት የግብይትና ጥራት ቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከር የባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የገበያ ትስስር ለማጠናከር በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ በዘርፉ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በመለየት ለመፍታት መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በክልሉ በተለያዩ ፓኬጆች ከ560 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በቡና መሸፈኑን የገለፁት አቶ አስራት በዚህም ከ513 ሺህ በላይ አርሶአደሮች በቡና ልማት እየተሳተፉ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በክልሉ ሁሉም አከባቢ የሚመረተውን የቡና ምርት ጥራቱን በማስጠበቅ ጤናማ የግብይት ስረዓት እንዲከተል በማድረግ ለሀገር የሚያስገኘው አስተዋጽኦ ማረጋገጥ እንደሚገባ ያነሱት አቶ አስራት በቡና ምርት ዝግጅትና ግብይት ዙሪያ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በቶሎ መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በምርት ዘመኑ ግማሽ ዓመት 30 ሺህ ቶን የሚጠጋ የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የተናገሩት አቶ አስራት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 67 ሺህ ቶን የቡና ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከቅመማ ቅመምና የሻይ ልማት አኳያ ክልሉ እምቅ አቅም እንዳለው የዘረዘሩት ኃላፊው በዘርፉ በቀጥታ የገበያ ትስስርና የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የታየው ውጤት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
አስተባባሪ ግበረ-ሀይሉ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መሠረት የሆነውን የቡና ምርት በተገቢው መንገድ መምራትና ምርታማነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ የጠቆሙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አማካሪና የግብርና ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሀንስ መላኩ የምርት ጥራቱን ከማስጠበቅ በተጨማሪ የግብይት ስርዓቱን ጤናማ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርት በጥራትና በብዛት ተዘጋጅቶ ለገበያ እንዲቅረብ ከአሊሚዎች ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
እአስተያየት ሰጪዎቹ ጤናማ ያልሆነ የገበያ ውድድርና የግብይት ስርዓት መላላት የዘርፉ ማነቆዎች በመሆናቸው ግብረ-ሀይሉ አጽንኦት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
በምክክር መድረኩ ከግበረ ሀይሉ በተጨማሪ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
