




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በቦንጋ ብዝሃ ዋና ከተማ ለሚነገቡ የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና የክልል ተቋማት ቢሮ ህንጻዎች ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነሥርዓት ላይ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉት፤ በቦንጋ ብዝሃ ዋና ከተማ የሚገነባው የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት እና ሌሎች የክልል ተቋማት ቢሮ ህንጻዎች ግንባታ በ2.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ግንባታዎቹ በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚጠናቀቁ መሆናቸውን አንስተው የክልል ተቋማት ህንጻ ከመሬት በታች አንድ ወለል እና ከመሬት በላይ ሰባት እንዲሁም የርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ህንጻ ከመሬት በታች ሁለት ወለል እና ከመሬት በላይ ባለሶስት ወለል ግዙፍ ህንጻዎች ናቸውም ብለዋል።
ለህንጻ ግንባታ የሚውል በጀት አሰባሰብ ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ያሉት ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ ከዚህ ውጭ በሚዛን አማን፣ቲፒ እና ታርጫ ብዝሃ ዋና ከተሞች ለሚገነቡ የክልል ተቋማት ህንጻዎች የመሠረተ ድንጋይ ቀጣይ እንደሚቀመጥና ሥራ በይፋ የሚጀመር መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከአራቱ ብዝሃ ማዕከላት ውጪ በሆኑት ክልል ተቋማት አገልግሎት የሚውል ህንጻ ለመገንባት የድዛይን ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን እነዚህም የክልሉ የበጀት አቅም በፈቀደ መልኩ ወደ ሥራ የሚገቡ ይሆናሉም ብለዋል።
በክልሉ ለመንግስት እና ለህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዲቻል እየተሰራ ያለው የተቋማት ግንባታ ሥራዎች እና ሌሎች የልማት ሥራዎች ተጠናክሮ ይቀጥላሉም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በከተማው የሚገነቡ ህንጻዎች የከተማን ውበት ከመጨመር ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ ዞኑና ከተማ አስተዳደሩ ለሥራው የሚውል ቦታ እንዲመቻች ወሰን በማስከበርና ይዞታን ነጻ በማድረግ ረገድ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
በስነሥርዓቱ ላይ የካፋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው የህንጻው መገንባት ለከተማው ተጨማር ውበት ከመስጠት በተጨማር የአከባቢውን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያነቃቃልም ብለዋል።
ለህንፃ ግንባታዉ በአካባቢዉ የሚገኙ 33 ነዋሪዎችን ልዋጭ ቦታ በመሠጠት የማንሳት ስራ መሰራቱን ገልፀዉ፣ ንብረት ቆጠራና ግምት ክፍያ እየተፈፀመ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሕንፃዉ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዞኑ አስተዳደር የሚያደርገዉን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ ኢንዳሻዉ፣ የአካባቢዉ ነዋሪዎችም ላደረጉት ትብብር አመሠግነዋል።
የመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነሥርዓት ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማንን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የካፋ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በፍቅር ከበደ
