የቤንች ሸኮ ማህበረሰብ ቴሌቪዝን ለማቋቋምና ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

Spread the love

የቤንች ሸኮ የማህበረሰብ ቴሌቪዥንን ለማቋቋምና ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ዞናዊ አብይና ንዑሳን ኮሚቴ ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን በመድረኩ እንደተናገሩት ሚዲያ የዲሞክራሲ ስርዓት ለማጠናከር ፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ፣ የገጽታ ግንባታ ለመስራትና የህዝቡን የስራ ባህል ለማሳደግ አይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።

ሚዲያ ሀገራዊ ፣ ክልላዊና ዞናዊ የህዝቡን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስራዎች ውስጥ ህዝቡን አሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

የህዝቡን ቱባ ባህል ፣ ታሪክ ፣ እሴቶችና የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለአለም ህዝብ ለማስተዋወቅ ወሳኝ በመሆኑ ወደ ስራ ውስጥ እየተገባ ይገኛል ብለዋል።

የሰፊውን አርሶ አደር የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፣ አብሮነትን እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ማህበረሰብ አቀፍ ቴሌቪዥን በጥራትና በፍጥነት ወደ አየር መውጣት እንዲችል የተደራጀና የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደግፌ ኩድን በመድረኩ እንደተናገሩት የሚዲያ ቴክኖሎጂን ሳይንሳዊነት ማስፋት ፣ ለሰው ኃይልና ይዘት ቅድሚያ መስጠትና ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ በበኩላቸው ሌሎች ሚዲያዎች እንዴት ተቀባይነት አገኙ የሚለውንና በአንጻሩ ለአንዳንድ ሚዲያዎች ውድቀት ምንድነው የሚለውን ልምድ በመውሰድ ወደ ስራ መግባት ይገባል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙባረክ አበበ በመድረኩ ባቀረቡት ሰነድ የህዝቡን መረጃ የማግኘት ህገ መንግስታዊ መብት እውን ለማድረግ የዞኑ መንግስት የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ለማቋቋም ቀድም ተብሎ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በቅድመ ዝግጅት የመመስረቻ ጽሁፍ ፣ መተዳዳሪያ ደንብ ፣ መዋቅር እና ፍቃድ የማግኘት ስራ ተሰርቷል ያሉት ኃላፊው በቅርቡም የስቱዲዮ ግንባታ ጨረታ ወጥቷል ብለዋል።

በቀጣይም የቴሌቪዥን ጣቢያውን እውን ለማድረግና ወደ ስራ ለመግባት አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን ማዋቀር በማስፈለጉ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ አካላት እንደተናገሩት የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያው ለዞኑ ህዝብ ወቅታዊ መረጃን ለማድረስ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የተቋቋመው አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች በተገደበ ጊዜ ውስጥ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አብዛኛው የሀገራችን ሚዲያዎች በቴክኖሎጂና ዘመኑን የዋጁ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ያላቸው ቢሆንም ይዘት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ ብዙም ተወዳጅ አይደሉም ብለዋል።

በዚህም ብቃትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን መያዝ ፣ ይዘት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ማለታቸዉን የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *