






በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች መምህራን ማህበር አዘጋጅነት ሁለተኛው ክልላዊ የትምህርት ጥራት ኮንፈረንስ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የክልሉ መምህራን ማህበር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በማድረግ እስከ ትምህርት ቤቶች ላይ በማውረድ ተግባራዊ እንዲደረግ እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አካሉ ዓለማየሁ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት እጅግ አሳሳቢ የሆነውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ ማህበሩ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ዕለታዊ ተግባሩ በማድረግ ግዴታውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ መምህራን ማህበር 5 ዓላማዎች ያሉት እንደ መሆኑ መጠን የክልሉ መምህራን ማህበርም እነዚህ ዓላማዎች ከዋና ጽ/ቤቱ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ወጥ ሆነው ሳይሸራረፉ ሊተገበሩ እንደሚገባ ያምናል ብለዋል።
ማህበሩ ከአባላት መብትና ጥቅም፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች እንዲሰጥ ከማድረግ ባሻገር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ በየደረጃው ካሉ የማህበራችን አደረጃጀቶች እንደሚጠበቅ አቶ አካሉ አሳስቧል።
መድረኩ ላይ ተገኝተው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ምዕራብ ክልል የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የክልሉ የመማር ማስተማር ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነመ እንዳሉት ጥናትና ምርምር በትምህርት ጥራት ላይ የሚታየውን ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት ትምህርት ሴክተር ሰፊ ክፍተቶችን አስተናግዷል ያሉት ምክትል ኃላፊው ይህን ክፍተቶችን ለመሙላት የፈተና ስርዓት የማዘመን፣የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም፣የትምህረት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ተግባር ላይ የተመሰረተ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ደስታ ገነመ የተማሪዎችን ውጤትና ስነ-ምግባር ማሻሻል፣የመማር ማስተማር ውጤታማነት ፣የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል፣የተማሪዎችን ተሳትፎ ማሳደግና የትምህርት ቤቶች ውስጣዊ ብቃት ማሳደግ በጥናትና ምርምር ማዳበር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል ሲል የዘገበዉ የካፋ ዞን የመንግስት ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።
