የክልሉ ግብርና ቢሮና ተጠሪ ተቋማቱ የ2016 በጀት ዓመት ያለፉት 11 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ገመገሙ፡፡

Spread the love

የክልሉ ግብርና ቢሮና ተጠሪ ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት ያለፉትን 11 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም መድረክ በቦንጋ ከተማ በጋራ ገምግመዋል፡፡

በመድረኩ በክልሉ ግብርና ቢሮና ተጠሪ ተቋማት በዋና ዋና ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ መልኩ የተፈፀመ መሆኑ ተገምግሟል፡፡

በእርሻ ዘርፍ ባለፉት 11 ወራት በዓመታዊና በቋሚ ሰብሎች ከምርት አኳያ የተለያዩ እድገቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በክልሉ ባለፉት 11 ወራት 855 ሺህ 569 ሄክታር ማሣ በዘር በመሸፈን 52 ሚሊየን 556 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ 97ሺህ ሄክታር ማሣ ምርት በሚሰጥ በቋሚ ሰብሎች በመሸፈን 23 ሚሊየን540 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ማግኘት የተቻለ መሆኑን አቶ ማስረሻ በላቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ባለፉት 11 ወራት ብቻ በዓመታዊ እና በቋሚ ሰብሎች 80 ሚሊየን ኩንታል የሚጠጋ ምርት የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች የነበረው መሆኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ በላቸው ምርትና ምርታማነትን ለማምጣት ያልታረሱ መሬቶችን እንዲታረሱ ለማድረግ በስፋት የተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የተለያዩ የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አይናተኛ መፍትሔ ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ማስረሻ፡፡

እስከአሁን 148ሺህ 690 ኩንታል በላይ አፈር ማዳበሪያ በመጠቀም 195 ሺህ ሄክታር የሚሆን ማሣ ላይ ቴክኖሎጂ እንዲዳረስ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በእንስሳት እና አሳ ሀብት ልማት ዘርፍ የሌማት ትሩፋትን ማነሻ በማድረግ የወተት፣ የእንቁላል እና የማር ምርት የማሣደግ ስራዎች በስፋት የተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ክልላዊ የወተት ምርትን 343 ሚሊየን ሊትር እና የእንቁላል ምርትን 227 ሚሊየን ማድረስ የተቻለ ሲሆን 70 ሺህ 434 ቶን የማር ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ ተችሏል ብለው 10 ሚሊየን በላይ እንስሳትን የመከተብ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ለአረንጓዴ አሻራ 210 ሚሊየን የሚጠጋ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸውን ችግኞች በማዘጋጀት ተከላ ለማካሄድ ተቅዶ እስከአሁን 191 ሚሊየን ችግኞች ለተከላ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

ከተዘጋጁት ችግኞች 48 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን እና ቀሪዎቹ 132 ሚሊየን ችግኞች በቀጣይ ሀምሌ ወር በሚደረገው አርንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ከመሬት አስተዳደር አንፃር 122 ሺህ 460 በላይ ማሣዎች የሁለተኛ ደረጀ የመሬት ልክቶሽ ስራ በመስራት ለ68 ሺህ 136 ማሣዎች የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱን አቶ ማስረሻ ጠቅሰዋል፡፡

ከቡና ምርት አኳያ 22ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን የቡና ማሣ በማስፋት የክልሉን የቡና ሽፋን 582ሺህ 136 ሄክታር ማድረስ የተቻለ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በክልሉ ከዚህ በፊት የአፈር ማዳበሪያ ዉዝፍ ዕዳነት የሚታየውን 582 ሚሊየን 950 ሺህ 7መቶ ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ስራን ታሳቢ ያደረገ የፈፃሚዎችን አቅም የማጎልበት ስራ፣ የቴክኖሎጂ ስርጸት ችግር ለመፍታት የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ስራ እና የኑሮ ውድነትንና አንደንድ ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጉዳይ በልዩ ትኩራት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የቢሮውና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ከየዘርፉ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *