









እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በግብርና ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የሚበረታቱ ናቸው ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሀገራዊ ተልዕኮን በመያዝ በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳዩ መጥተዋል፡፡
በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ ከ346 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በዘር በመሸፈን 17.5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ምዕራብ ኢትየጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል ፡፡
በክልሉ ከታቀደው 346 ሺህ 343 ሄክታር ማሳ ውስጥ 99 በመቶ የታረሰ መሆኑንና ከዚህም 85 በመቶ የሚሆነው በዘር መሸፈኑ የሚበረታታ ስራ መሆኑም ተጠቅሷል ፡፡
የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፋ ለክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሪፖርተር እንደገለፁት በ2016/17 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ 346 ሺህ 343 ሄክታር ማሳ በዘር በመሸፈን 7.5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በአዝዕርት ሰብሎች ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡
በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ 99 በመቶ የሚሆነው መታረሱንና ከታረሰው መሬት ውስጥ 294 ሺህ ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈኑን ያብራሩት አቶ አሸናፊ አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም በማድረግም 105 ሺህ ሄክታር ማሳ በመስመር እንደተዘራ አስታውቀዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከክልሉ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀትም 107 ሺህ 215 ኩንታል የአፈር ማዳበሪ መሰራጨቱን የጠቀሱት ኃላፊው ከምርጥ ዘር አቅርቦት አኳያም 25 ሺህ 15 ኩንታል የተመሰከረለት ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች መቅረብ መቻሉንም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ በስፋት የባቄላና አተር ሰብሎች በመኸር እንደሚለማ የጠቀሱት አቶ አሸናፊ 10 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘርና 14 ሺህ ሳቼት / ህያው ማዳበሪያ/ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱንም ጨምረው ገልጸዋል ፡፡
የኩታ ገጠም እርሻ ተግባራዊ ከማድረግም አኳያ 90 ሺህ ሄክታር ታቅዶ በ455 ቀበሌዎች በተፈጠሩ 2970 ክላስተሮች 86.5 ከመቶ ማሳ በዘር ተሸፍኗል ያሉት አቶ አሸናፊ በክልሉ በሚገኙ 16 ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች 22 ሺህ ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 16 ሺህ ሄክታር ማሳ በዘር መሸፈኑንና ለዚህም አስፈላጊው ግብኣቶች መቅረባቸውን ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በሆርቲካልቸር ሰብሎች 45 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገን የገለጹት አቶ አሸናፊ 72 ከመቶ የሚሆነው ማሳ መታረሱንና ከዚህም ውስጥ 67.5 በመቶ በዘር መሸፈኑን እንዲሁ ገልጸዋል ፡፡
ምርትና ምርታመነትን ለማሳደግ በበጋው ወቅት የተዘጋጀ ኮምፖስት በተቀናጀ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ የተናገሩት ኃላፊው በክልሉ በተከናወነው የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ 12541 ሄክታር የሚሸፍን ፍራፍሬ መተከሉንና 550 ሄክታሩ በክላስትር መልማቱን አብራርተዋል፡፡
በመኸር እርሻ የተዘሩት ሰብሎች በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኙና ቀደም ብለው የተዘሩት ሰብሎች በአበባ ደረጃ እንደሚገኙም አቶ አሸናፊ አክለው ምርታማነትን በማሳደግ በኩል የምርት መቀነስን ሊያስከትሉ የሚችሉ የተባይ አሰሳና የአረም ቁጥጥር ስራዎች በተቀናጀ መንገድ የክልል ባለሙያዎች በዞን ደረጃ ተመድበው ድጋፍና ክትትል ስራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡
ክልሉ በስንዴ ሰብል በስፋት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አሸናፊ 30 ሺህ ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝና በሰብሉ ላይ የስንዴ ዋግ አሰሳ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በካፋና ሸካ ደጋማ ቦታዎች የሳታላይት መረጃን መሰረት ያደረገ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችም በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት አቶ አሸናፊ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዩሪያ ያለውን ጠቀሜታ አርሶ አደሩና ባለሙያው በተገቢው በመገንዘብ ትኩረት አድርገው ጥቅም ላይ እነዲያውሉ አሳስበዋል፡፡
በነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በክልሉ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ቦሎቅ የሚዘራባር ወቅት በመሆኑ አርሶ አደሩ በተገቢው መንገድ ማሳውን በማዘጋጀት ዘሩን በወቅቱ መዝራት እንደሚገባውም ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ በቦሎቄ ሰብል 40 ሺህ ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈንም በትኩረት እየተሰራ እንዳለም የገለፁት አቶ አሸናፊ በመኸር ቀሪ እርሻ ወቅት የቀበሌ ግብርና ልማት ሰራተኞች አርሶ አደሩ የቤተሰብ ጉልበትን በመጠቀምና በተፈጠሩ አደረጃጀቶች የአረምና የተባይ ቁጥጥር ስራዎችን በማጠናከር የተሸለ ምርት ለማግኘት እንዲችሉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
በክልሉ በመኸር እርሻ ወቅት በምርት ዘመኑ በአዝርዕርትና በሆርቲካልቸር ሰብሎች 17.5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
በታጠቅ አበበ
