በትኩረት መልማት የሚገቡ የዘመን መለወጫ በዓላት!

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 13 ነባር ብሔር/ብሔረሰቦች የሚገኙበት በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ባህላዊ ዕሴቶችና ቅርሶች ያሉበት የብዙሃ ባህል፣ ትውፊትና ታርክ ባለቤት ነዉ፡፡

የክልሉ ብሔር/ ብሔረሰቦች የራሳቸው የሆኑ የተለያዩ ታርካዊ፣ ባህላዊና ሐይማኖታዊ በዓላትና የቀን አቆጣጠር ስልት ያላቸዉ መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል።

ከነዚህ ባህላዊ ዕሴት መገለጫዎች መካከል አንዱ የሆነዉና በተለያየ ጊዜ በልዩ ልዩ ኩኔቶች የሚከበረዉን ብሔር/ ብሔረሰቦች  የዘመን መለወጫ በዓላትን በወፍ በረር ለማቅረብ እንወዳለን፡፡

የካፈቾ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መለወጫ በዓል ማሽቃሬ ባሮ(የቤነ ሻዴዬ ባሮ) በመባል ይታወቀቃ፡፡ የብሔረሰቡ የዘመን ለዉጥ የክረምንት ወራትን ተከትሎ ይታደሳል፡፡

በክረምት ወቅት በካፋ ምድር የሚገኙ ወንዞች ይሞላሉ፤ ወትሮውኑ መገለጫው የሆነው የአከባቢው  ልምላሜ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ የካፈቾ ብሔር ማሽቃሬ ባሮ አዲስ ዓመት ከገበሬዉ የእርሻ ስራ ጋር የተያያዘ ሲሆን መለያዉም ከመዝራት፣ ከዕድገትና ከመኸር ዑደት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የብሔሩ አባላት በተለያዩ ባህላዊና ትዉፍታዊ ክዋነዎች የካፋ ንጉስ መቀመጫ በነበረውና በየዓመቱ በዓሉ በሚከበርበት “ቦንጌ ሻንቤቶ” በሚባለዉ ስፍራ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ፡፡ የዘመን መለወጫ በዓሉ የብሔሩ አባላት በጉጉት የሚጠብቁትና ከአሮጌዉ ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገሩበትና አዲስ ተስፋ የሚሰነቅበት ህዝባዊ በዓል እንደሆነ ይነገራል፡፡

“የቤነ ሻደዬ ባሮ/ ማሽቃሬ ባሮ”ን ከ1897 በፊት በነበረዉ በካፋ ንጉስ ጊዜ ጀምሮ በየዓመቱ ከሁሉም የካፋ ወራፎች ወደ ቦንጋ ከተማ ቦንጌ ሻምበት በመምጣት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ በዓሉ 100 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት እየተከበረ የሚገኝ አንደሆነ የዞኑ ባህል ተርዝምና ስፖርት መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

በዓሉ በዓመት ዉስጥ የተሰራ ስራ የሚገመገምበት፣ አዳድስ ሹመት የሚሰጥበት፣ የተሰጠዉን ኃለፊነት በአግባቡ ያልተወጡ የሚወርድበት እና በበዓሉ ላይ የተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦችን በልተዉ፣ ጠጥተዉ፣ ጠግበዉ፣ ተደስተውና ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት በዓል ነዉ።

የበዓሉ አከባበር ስርዓት የእርሻ አዝመራን ተከትሎ ሐምሌ 5ን መነሻ በማድረግ የሚቆጠር ሲሆን 77 ቀን እየተባለ ሄዶ እየተቆጠረ 77ኛዉ ቀን ሲያልቅ የሚከበር በባህላዊ የቀን አቆጣጠር ላይ ተመስርቶ  በከፍተኛ ደስታ የሚከበር የአዲስ ዓመት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በክልሉ ከሚገኙት ነባር ብሔረሰቦች መሀል የዳውሮ ብሔረሰብ አንዱ ነው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓሉም “ቶክ በኣ” ሲሆን የዳዉሮ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ቀን አቆጣጠር ጥበብ ያለውና የጨረቃ መታየትንና መጥለቅን ተከትሎ አሮጌዉን ዓመት ሸኝተው አድሱን የሚቀበሉበት ትልቅና ደማቅ የዘመን መለወጫ በዓል ነዉ፡፡

“ቶክ በኣ” ጥረ ትርጉሙ መዝኖ ማየት ሲሆን በዕለቱ ሰዉና እንሰሳት ጠግበው ካላደሩ ግለሰብም ሆነ ሀገሩ ይራባል የሚል የብሔረሰቡ ብህል ሲሆን በዉስጡም በአድስ ዓመቱ በምግብ ራስን መቻል ወይም ጥጋብን፣ ዕርቅን፣ ሠላምን፣ ደስታን፣ ጠንክሮ መስራትን፣ መደጋገፍንና የመሳሰሉ መልካም ዕሴቶችን የያዘ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዳዉሮ ብሔረሰብ ዘንድ ለበዓሉ አከባበር የተለያዩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች የሚዘጋጁ ሲሆን በዕለቱ የሰዉ ልጆች ጠግቦ ያድራሉ፤ ለከብቶቻቸዉ አስቀድሞ ሣር ይዘጋጃል፤ ጆኒያዎች በእህል፣ እንስራዎች በዉሀ ተሞልተው የሚያድሩበት የጥጋብ ምኞት ማሳያም ጭምር ነዉ።

ዳዉሮዎች በዓሉን ሲያከብሩ በለያዩ ቦታ ያሉት የብሄሩ ተወላጆች በመሰባሰብ ካላቸዉ በማካፈል፣ ያጡትን በመርዳት፣ የተጣሉትን “በዱቡሻ” ስርዓት በማስታረቅ በዓሉን ከማክበርም በላይ የተለያዩ ቅርሶችንና ባህላዊ ዕሴቶችን የሚያስተዋወቁበት ትልቅ መድረክ ነዉ፡፡

ቶክ በኣ ከመከበሩ በፊት በብሔረሰቡ አባላት የተለያዩ ዝግጅቶች የሚከናዎኑ ሲሆን እናቶችና አባቶች፤ ልጃገረዶችና ወጣቶች የራሳቸዉን የተለያየ የስራ ድርሻ ይከፋፈላሉ፡፡ በአሮገው ቀን መጨረሻና በአድሱ ዓመት መቀበያ ምሽት ከቤታቸው እሳትን ወደ ወጭ በመወርወር  ክፉ ሁሉ እንዲርቅ የሠላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የጥጋብ ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ይገልፃሉ።

የሸካቾ ብሔረሰብም የራሱ የሆነ “ማሽቃሮ” የሚባል የዘመን መለወጫ በዓል ያለዉ ሲሆን በዓሉ የሚከበርበት ቀናት በየዓማቱ ከመስከረም 17-30 ባለዉ ጊዜ ውስጥ እንደሆነ የዞኑ ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት መምሪያ መረጃ ያሳያል፡፡

የሸካቾ ብሔረሰብ በዓሉን ሲያከብር ዓመቱን ሙሉ የጠበቀዉን ፈጣሪ ለማመስገን፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር፤ አዳድስ የሚወጡ ባህላዊ ህጎችን ለማጽደቅ፤ ቀድሞ የነበሩ ህጎችን ለመሻር እና ሌሎች ጉዳዮችን ለማከናወን እንደሆነ የመምሪያዉ መረጃ ያመለክታል፡፡ በዓሉ የተለያዩ ክዋኔዎችና ዝግጅቶች የሚቀርቡበት ሲሆን  የጎረቤት ብሔር/ብሔረሰቦችን በመጋበዝ እንዲሁም የሸካቾ ብሔረሰብ አባላት ካሉበት ሁሉ በመሰብሰብ በአንድ ላይ የሚያከብሩበትና “ቲሞ እና ሸሮ” የሚጸድቅበት ነዉ፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ ባህላዊ ጭፈራ፤ ባህላዊ የሸካቾ ምግብና መጠጥ እንድሁም የባህላዊ ቅርሶች ኢግዚብሽን ለታዳሚዉ ይቀርባል፡፡  የበዓሉ ተሳታፊዎችን በሚመለከት የሸካቾ ብሔረሰብ ንጉስ፤ የምክረቾ አባላት፤ ከጎረቤት ኦሮሚያ አባገዳዎች፤የከፋ ንጉስ ከነምክረቾ እና ሌሎች የጎረቤት ብሔረሰቦች ተወካዮች እንድሁም የሸካቾ ብሔረሰብ ተወላጆች በሙሉ ይሳተፈሉ።

በመሆኑም በዓሉ ለአብሮነት፤ አካታችነት፤ አንድነትና ህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲሁም ከሩቅም ከቅርብም ያሉት የሚሰበሰቡበት በመሆኑ ዘመድ የሚገናኙበትና የሚደሰቱበት በመሆኑ ባህላዊ መስተጋብር የሚፈጥር በዓል ነው፡፡

ፋይዳዉም የሸካቾ ብሔረሰብ ከጥንት ጀምሮ ያለዉን ባህልዊ የአስተዳደር ስርዓት ለማሳየት፤ የመከባበርና የመቻቻል ባህሉን እንዳይረሳና ለቀጣይ ትዉልድ ለማስተላለፍ፤ ዘመናዊ የፖለቲካ አደረጃጀት ከመምጣቱ በፊት የራሱ ምክር ቤት እንደነበረዉና ለዘመናዊዉ ፖለቲካ መዋቅር መነሻ ከመሆኑም በላይ በየአካባቢዉ የሚነሳዉን ግጭት በራሱ አደረጃጀት እየፈታ የመጣ መሆኑን ለማመላከት እንዲሁም ፈጣሪን ለማመስገንና ለቀጣይ ለምርት ዓመት ውጤታማነትና ሠላም ፈጣርን የሚለመንበት መሆኑን ማሳያ በዓል ነዉ፡፡

ከካፈቾና ሸካቾ በተጨማሪ የቤንች ብሔረሰብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ነባር ብሔር/ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን የራሱ የሆነ የንግስና እና አስተዳደራዊ ስርዓት ያለዉ ሲሆን ጠንካራ የአከባቢ ጥበቃ ልምድ ያለዉ፣ የተለያዩ የማንነት መገለጫ ቱባ ባህል ባለቤትም የሆነ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ነዉ፡፡

ከነዚህ ቱባ ባህላዊ ዕሴቶች አንዱ የብሔረሰቡ የዘመን መለወጫ በዓል “ቢስት ባር” ነዉ፡፡ “ቢስት” ማለት በኩር ወይም ጅማሮ ማለት ሲሆን በክረምት የተዘራ እህል ደርሶ የመጀመሪያዉን ፍሬ በጋራ የሚቀምሱበት መሆኑን ያመለክታል። “ባር” ማለት ደግሞ በዓል ሲሆን በዓሉ በብሔረሰቡ ዘንድ ከፍ ያለ ትርጉምና ቦታ የሚሰጥ ለሰዉ ልጆች ተገቢ ክብርና ፍቅር በመስጠት፣ በመከባበር፣ በመተሳሰብና  በመደማመጥ የሚያከብሩት በዓል መሆኑን የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ መረጃ ያሳያል፡፡

በዓሉ ወደ አድስ የዘመን ምዕራፍ መሸጋገርን የሚያበስር የዝናብ ወቅት አልፎ የበጋ ፀሀይ ወቅት መሻገሪያ የተዘራዉ እህል ደርሶ በጋራ ተሰብስቦ ለደረሰዉ እህል ፈጣሪያቸዉን የሚያመሰግኑበት፤ ለቀጣይ አዝመራ መልካምነትና ለቤተሰብና ጎረቤት ጤንነት መልካም ምኞት፤  ለሀገር ሠላም ጸሎታቸዉን በማድረስ የሚመረቁበት፤ የተጣሉት የሚታረቁበት፤ የመተሳሰብና የመደጋገፍ የምስጋና በዓል ነዉ። በበዓሉ ጊዜ ቤንቾች ያመረቱት እህል ደርሶ አብሮ የሚበሉበት፤ አለመግባባትና ግጭት የሚፈታበት፤ የተበደለዉ የሚካስበት፤የአብሮነት መገለጫ በዓል ነዉ፡፡

በቢስት ባር ከመጀመሪያዉ እህል የተዘጋጀዉን ምግብም ሆነ መጠጥ የመጀመሪያ ልጅ ወይም ታላቅ ሳይቀምስ ሌሎች ታናናሾች መመገብ አይችሉም።

 የቢስት ባር ለትዉልድ መከባበርን በማስተማርና የባህላዊ ስርዓት ሰንሰለቱን ለቀጣይ ትዉልድ ከማስተላለፍ ጋር ተያይዞ የሚከበር በዓል ሲሆን ለበዓሉ የተዘጋጀዉ ምግብና መጠጥ የበኩር ልጅ እንዲቀምስ በዕድሜ ደረጃ ከታላቅ እስከ ታናሽ በተራ ከመድረሱም ባሻገር ከቤተሰብ አልፎ ለጎረቤት እዲደርስ ይደረጋል።

በበዓሉ ዕለት የቤንች ልጆች በዓመት አንድ ጊዜ ከሌሊት ጨረቃና ከዋከብት ጋር ደስታቸዉን የሚጋሩበት ልዩ ቀንም ነዉ ቢስት ባር፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀ ምግብ እየበሉና ቦርዴ እየጠጡ ከሽማግሌዎች ጋር የምስጋና  ስነ ስርዓትን እንያከናወኑ ወደ ውጭ ወጥተዉ በጨረቃ ብርሃን እየጨፈሩ የሚያከብሩት የአብሮነት በዓል ነዉ።

ሌላው በክልሉ ከሚገኙት ነባር ብሔር/ ብሔረሰቦች አንዱ ሸኮ ነው፡፡ የሸኮ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ ባህል፣ ወግና ታርክ ያለዉ ህዘብ ነዉ፡፡ የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ቲከሻ ቤንጊ” የአንድነትና የግበዣ በዓል ሲሆን የክረምት ወራት አልፎ በጋ የሚተካበት፣ የማሽላ ምርት የሚገባበት፣ ግራዋ የሚያብበትና የግራዋ ማር የሚቆረጥበትና የደረሱ ምርቶች ከተሰበሰቡ በኃላ የሚከበር በዓል እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በዓሉ እርቅን፣ አብሮ መኖርን፣ ባህላዊ ዳኝነትን  የሚያጠናክር የብሔረሰቡ ታላቅ በዓል ሲሆን በማህበረሰቡ ስነ ልቦና የነበረና ለረጅም ጊዜ ሳይከበር የቆዬ ነገር ግን የቀድሞ አባቶችን ፈለግ በመከተል በ2016 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ እንደገና ማክበር የተጀመረ በዓል ነዉ፡፡

በመሆኑም ይህ በዓል የሸኮ ብሔረሰብ በወርሃ ጥር የአዲስ ዓመት አድስ ተስፋ በመሰነቅ ያለፈዉን ዓመት በሠላምና በጤና ላሻገራቸዉ ፈጣሪ በጋራ ተሰብስቦ ምስጋና የሚያቀርቡበት ትዉልድ ተሸጋሪ በዓል ነዉ።

እንደ ሸኮ ሁሉ የኮንታ ብሔረሰብም “ህንግጫ” የሚባል የዘመን መለወጫ በዓል ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ወደ ትውል ሲተላለፍ የመጣ ከአሮገዉ ዓመት ወደ አዲሱ የሚሸጋገሩበት  በዓል አለው፡፡ የህንግጫ በዓል አጠራሩ ያማረ፣ ያገጠ፣ የለመለመ የሚል ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን አደይ አበቦች ፈክተዉ የሚታዩበት የክረምት ወራት አልፎ የጠራ ሰማይ በሚታይበት ወቅት የሚከበርበት በዓል መሆኑን የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

በዓሉ የተጣሉት የሚታረቁበት፣ የተለያዩት የሚሰበሰቡበት፣ አርሶ አደሮች የክረምት አዝመራቸዉን አገባድደዉ ከአረምና ኩትኳቶ ስራ አርፈዉ ለመልካም ፍሬ ተስፋ የሚሰንቁበት ወቅት በመሆኑ በብሔረሰቡ ዘንደ በልዩ ትኩረትና ተስፋ የሚከበር በዓል ነዉ ህንግጫ፡፡

የህንግጫ በዓል ሲከበር በዕለቱ ሁሉም ጠግበዉ፣ ጎዶሎዉ ሞልቶ፣ መጥፎ ነገር ሁሉ ቀርቶ መልካም መልካሙ እንዲሸጋገር ፈጣሪን የሚለምኑበት የጥጋብና ሙሉ የመሆን አስተምህሮ  የሚገለጽበት የተስፋ በዓል ሲሆን ከጳጉሜን መጨረሻ እስከ መስከረም 17 ድረስ የሚከበር የኮንታ ዞን አዲስ ዓመት የልምላሜ መገለጫ ነው፡፡ በኮንታዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የህንግጫ በዓል የተስፋና የፍሰሐ ነው።

ከላይ የተገለጹ የብሔር/ ብሔርሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት በተለያየ ደማቅ ሁኔታ ለማክበር እንዲሁም በዓሉን ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ህዝባዊ ለማድረግ ከመንግስት ቋት በመላቀቅ በየዞኑ አበረታች ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ።

በተለያየ ጊዜና ኩኔት የሚከበሩ እነዚህ የተለያዩ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓላት በቋንቋና ባህል ዕድገት ላይ የራሱን አሻራ ከማሳረፍ ባለፈ በየዞኑ የሚገኙ የቱርዝም ሀብቶችን ለማስተዋወቅ  ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ መጥቷል፡፡

በመሆኑም  የብሔር/ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ የሆኑት ቱባ ባህልን ሆነ በዚህ ጽሁፍ ያልተካተቱ እና ገና ልለሙ ያሉትንም  መጠበቅ፣ ማልማት፣ ማስተዋወቅና ለትዉልድ ማስተላለፍ እዲሁም በጥናትና ምርመር ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት ነዉ።

መልካም የዘመን መለወጫ በዓል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *