






የተሀድሶ ስልጠናው የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ያዘጋጀው ሲሆን ለ8 ቀናት የሚቆይ መሆኑም ታውቋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ እንደተናገሩት የትራንስፖርት ዘርፍ ትልቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፍ ነው ብለዋል። ዘርፉ ከሰው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር በጥብቅ የተቆራኘና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይሁንጂ በተለይም በህዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ በየቀኑ የሚከሰተው የትራፊክ አደጋ በሰው ህይወት ፣ አካልና በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየአመቱ ለአሽከርካሪዎች የተሀድሶ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። እንደ ዞን ባለፉት ተከታታይ አመታት በተሰጠው ስልጠና ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም በተፈለገው ልክ አይደለም ብለዋል።
የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ ዘንድሮም ለነባርና አዲስ አሽከርካሪዎች የሚሰጠው ስልጠና በተለይም በአሽከርካሪ የስነ ምግባር ችግሮች ፣ የክህሎትና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳል ብለዋል። ከስልጠናው ማግስትም በትራንስፖርት ዘርፉ የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅም አቶ መስፍን ገልጸዋል።
የዞኑ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ደቦጭ በመድረኩ እንደተናገሩት ስልጠናው በዋናናነት በአዋጅ 557/2016 ላይ ያተኮረና አንድ አሽከርካሪ በስነ ምግባር ፣ በክህሎት ሊላበስ የሚገባው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።
እንደ ዞን ባለፉት አመታት በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የሚታዩ የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ ተችሏል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ከዚህ በላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ያለመ የተሀድሶ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል። በዘንድሮው ስልጠና በደረቅ ፣ በህዝብ ፣ በታክሲና በከተማ ትራንስፖርት ለተሰማሩ ከ4ሺ በላይ አሽከርካሪዎች በዙር የሚሰጥ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል ሲል የዘገበዉ የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነዉ።
