
በጥቅምት ወር ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ካለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላት በድምቅት መከበራቸውን አስታውሰዋል፡፡
በዓላቱ የሕዝቦችን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የአንድን ሀገር እምቅ ባህል እና እሴት በሚገባ ያንጸባረቁ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በተያዘው ጥቅምት ወር ኢትዮጵያ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ኮንፈረንሶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጓን ጠቁመው፤ በዚህ መሰረት ከረሃብ ነጻ የሆነ ዓለም ኮንፈረንስ ከጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ አንስተዋል።
በመድረኩ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 500 እንግዶች እንደሚሳፉ ይጠበቃ ነው ያሉት፡፡
በኮንፈረንሱ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በምግብ እራስን ለመቻል በተለይም በበጋ ስንዴ፣ በኩታ ገጠም እና በአየር ንብረት ለውጥ ሥራ ያላትን ተሞክሮ የምታካፍል ይሆናል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ስብሰባ ከጥቅምት 9 እስከ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
ጉባዔው ኢትዮጵያ በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት እቅድ ከመያዟ ጋር ተያይዞ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አስገንዝበዋል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።
