




የዘንድሮው አለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ለ13ኛ ጊዜ “ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው” በሚል መሪ መሪ ቃል በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ታዳጊ ሴት ልጆች እየተጋፈጡት ያለውን ፈተና እንዲሻገሩ ለማስቻል በጋራ መረባረብና ትኩረት ሰጥተን መሰራት ይገባናል ብለዋል።
ዛሬ ያልዘራነውን ነገ ማጨድ አንችልም ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ የተሻለች ሀገር ለመገንባት ታዳጊ ሴቶች ላይ ዛሬ መስራትና ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የፆታ እኩልነትን ለማስፈን እንዲሁም ሴቶችን ለማብቃት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ወደፊትም በሴቶች መብት ዙሪያ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።
ታዳጊና ወጣት ሴት ልጆችም አቅማቸውን እንዲያጎለበቱ፣ ጠንካራ ስነ-ልቦና እንዲያዳብሩ፣ ታላቅ ህልም ማለምና ትልልቅ አላማዎችን ለማሳካት እንዲተጉ መክረዋል።
ህልማቸውን ከሚያደናቅፉ እና ከትምህርት ገበታቸው ወደ ኃላ እንዲቀሩ ከሚያደርጉ የአቻ ግፊቶችም እንዲጠበቁ አደራ ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ የወደፊት ተስፋ በመሆናቸው ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም ትልቅ ነገርን ማስመዝገብና ማሳካት እንዲችሉ መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
