
የጤና ሚኒስቴርና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ወደ ማህበረሰቡ ለሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
መንግስት የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ እየሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ ከማስፈታት ጀምሮ መልሶ የማቋቋም ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ይገኛል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን ለሰላምና ምርታማነት ለማዘጋጀትም ማህበራዊ ተሃድሶ፣ አዕምሯዊ ዝግጅትና ግንዛቤ መስጠት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም እንዲሁ፡፡
ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫም የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው የተሐድሶ ሂደት ውስጥ በመቀላቀል የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውንም በሀገራዊ ምክክር ሂደት በመሳተፍ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዛሬው እለትም የጤና ሚኒስቴርና የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ወደ ማህበረሰቡ ለሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረትም ማህበረሰቡን የሚቀላቀሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የሥነ-ልቦና ምክርን ጨምሮ የተሟላ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚቻል ይሆናል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አየለ ተሾመ (ዶ/ር)፤ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በሚሰማሩበት ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ የጤና ሁኔታ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም ለቀድሞ ታጣቂዎች የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ የቀድሞ ታጣቂዎች ተመልሰው ለሀገር የሚጠቅሙ አምራች ዜጎች እንዲሆኑ የሁሉም እገዛና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ታጣቂዎች ጤናቸው ተጠብቆ የተስተካከለ ሕይወት እንዲመሩ የሚያስችል ስለመሆኑ አንስተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
