መንግስት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዟል – የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

መንግስት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለፁ።
ለመንግስት ሰራተኞች ከመስከረም 2018 ዓ.ም ጀምሮ የደመወዝ ማሻሻያ መደረጉም ተመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ወደ ሙሉ ትግበራ ማስገባቱን ተከትሎ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ዕውቅና ተሰጥቶታል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለፁት፥ መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያካሄዳቸው ዘርፈ ብዙ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።
በተለይም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ዓይነተኛ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በተለይም የዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን ጫና ውስጥ እንዳይከት መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱንም አስታውሰዋል።
መንግስት የቋሚ ደመወዝ ተከፋይ ዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከመስከረም ጀምሮ የተደረገው ማሻሻያም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሸን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የመንግስት ተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር በማዘመን በክህሎትና በባህሪ የበቃ የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማትን በመዘርጋት ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ሪፎርሞች እየተካሄዱ ናቸው።
የማሻሻያ ሪፎርሙ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ በስምንት ተቋማት በደረጃ ሲተገበር እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከተቋማቱ መካከል የገንዘብ ሚኒስቴር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ጨርሶ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሙሉ ትግበራ መግባቱን አድንቀዋል።
ሚኒስቴሩ በአተገባበር ሂደት የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ለሌሎች አርአያ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ ተጨማሪ 160 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ይህም የመንግስትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የመንግስት ሰራተኛው ስራውን በውጤታማነት በመፈፀም ለአገራዊ ዕድገት የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ኮሚሽነሩ ሪፎርሙ የመንግስት ተቋማት አሰራራቸውን በማዘመን ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች መረጃዎችን ይከታተላሉን ![]()
በፌስቡክ https://www.facebook.com/sowestcommunication/
በድረገጽ www.southwestcomunications.gov.et
በኢንስታግራም https://instagram.com/southwest_communications
በትዊተር twitter.com/sweprs
በቲክቶክ https://www.tiktok.com/@southwest.communi
በቴሌግራም https://t.me/Debubmierab
በዩቲዩብ youtube.com/@southwestgovcommunication
በዋትስአፕ
https://whatsapp.com/channel/0029VbAiSCpGE56ue7VyJJ3x
በሊንክደን
