በክልሉ በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 56.55% ተማሪዎች ወደ ቀጣይ ክፍል ማለፋቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ

Spread the love

በክልሉ በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና 56.55% ተማሪዎች ወደ ቀጣይ ክፍል ማለፋቸውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ

ቢሮው በ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በክልሉ የ8ኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ 36 ሺህ 683 ተማሪዎች 20 ሺህ 744 ተማሪዎች ወደ ቀጣይ ክፍል ማለፍ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ይህም አምና ከተመዘገበው 42.39% የማለፍ ምጣኔ ዘንድሮ በ14% ጭማሪ መመዝገቡን አስረድተዋል።

አጠቃላይ ማለፍያ ነጥብ ለመደበኛ ተማሪዎች 50%ና ከዚያ በላይ ሲሆን ለአርብቶ አደር አከባቢና ለአካል ጉዳተኞች 46%ና ከዚያ በላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ተማሪ አቤኔዘር መርክነህ መንገሻ ከዳውሮ ዞን ገሳ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 98.57% በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡም በመግለጫቸው ተካትቷል።

አጠቃላይ የማለፍ ምጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለፁት አቶ አልማው ከዘንድሮ ውጤት በመነሳት በቀጣይ በትምህርት ጥራት ላይ የሚሰሩ በርካታ ተግባራት እንዳሉም አስረድተዋል።

የፈተና አስተዳደር ስርዓቱ ከኩረጃና ስርቆት በፀዳ መልኩ የተሰጠበት እንደሆነም ያነሱት ሀላፊው ከፈተና ግብረ ሀይሎች ጋር የተደረገ የተቀናጀ አሰራር ውጤት አሰግኝቷል ብለዋል።

የትምህርት ግብአትን በበቂ ሁኔታ ማቅረብና የመምህራን አቅም ማሻሻያ ስራ በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚሰራ እንደሆነም አብራርቷል።

በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል መደበኛ ተፈታኞ 33,350 (59.13%)፣ የግል 2943 (33.4%) ፣ የማታ 67 (5.57%) እንዲሁም የርቀት 323 (11.5%) መሆናቸውም ተገልጧል።

ተማሪዎች ከዛሬ ጀምሮ በ sw.ministry.et ስማቸውንና የፈተና መለያ ቁጥራቸውን በማስገባት መመልከት ይችላሉ ብለዋል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *