



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ክልላዊ የክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ማድረግ ጀምሯል።
በንቅናቄው መድረክ የተገኙት የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ እንዳሻው ገበያ መር የክህሎት ልማትን እውን በማድረግ ሁለንተናዊ ብልጽግናን በማረጋገጥ ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ውጤታማ፣ዘላቂና ተቋማዊ በማድረግ ክልላዊ ተልዕኮን በብቃት ለመወጣት ቢሮውን በአዲስ አደረጃጀት አደራጅቶ ወደ ስራ መገባቱንም ተናግረዋል ።
አደረጃጀቶችን ተከትሎም የራስን አቅም አሟጦ በመጠቀም ያሉንን ውስን በጀት ወጪ ቆጣቢ በሆነ ዘዴ አብቃቅቶ በመጠቀም የላቀ ውጤት ለማምጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል ።
በተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ውጤታ እንዲሆንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ እና የተደራጀ በማድረግ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ይገባልም ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በሚደረገው የምክክር ውይይት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተደራሽነትና ፍትሐዊነት፣ቴክኖሎጂውን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ፣የቴክኒክና ሙያ ስርዓቱ የኢንተርፕራይዞች መፈልፈያና ዘላቂ የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት እንዲደረግበትም አቶ ተስፋዬ እንዳሻው አሳስበዋል ።
ትኩረት የሚሹ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራትን ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች ጋር በማስተሳሰርም መፈጸም እንደሚገባም አቶ ተስፋዬ እንዳሻው አጽንኦት ሰጥተውበታል ።
ቢሮው የየዞኖችን እና የቢሮውን የአንደኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም የሚገመግም ሲሆን ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ከድርጊት መርሃግብሩ ማወቅ ተችሏል።
በነገው ዕለትም ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚኖረው ውይይት በብድር አመላለስ እና የስራ ዕድል ፈጠራ ምክርቤት የንቅናቄ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።
በቦንጋ ከተማ በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ የቢሮው ኃላፊዎች ፣የዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊዎች ፣የኦሞ ባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆችና የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ዲኖችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።
በታጠቅ አበበ
