ታሪክና ባህልን በማልማት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና መጠናከር እንደለበት ተጠቆመ።

Spread the love

የካፈቾ ብሔር የዘመን መለወጫ (ማሽቃሬ ባሮ) በማስመልከት በተዘጋጀው የካፌቾ፣ የናይ እና የጻራ ብሔር ብሔረሰቦች የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም ተሳታፊዎች የካፋ ታሪክና ባህልን በማልማት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ሚና መጠናከር እንደለበት አንስተዋል።

በቦንጋ ከተማ በተካሄደው የካፈቾ፣ የናይ እና የጻራ ብሔር ብሔረሰቦች የባህልና ቋንቋ ሲምፖዚየም በካፊ ኖኖ፣ በናይ እና በጻራ ቋንቋና ባህል ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

በካፈቾ ብሔር ባህልና ታሪክ ላይ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማጠናከር ጠቃሚ ባህሎች ማሳደግ እንዲሁም ጎጂ የሆኑት ማስቀረት እንደሚገባ ያስገነዘቡት አስተያየት ሰጪዎቹ በተላይ የቡና መገኛ ማኪራን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ እንዳለበትም ነው ያነሱት።

የካፊ ኖኖ ቋንቋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት እያሳየ መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ ቋንቋውን በስነጽሁፍ ደረጃ በማሳደግ በኪነ ጥበብ መድረክ በስፉት ጥቅም ላይ ማዋል እንዲሁም በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ትርጉም ላይ ማዋል እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።

በብሔሩ ታሪክና ባህል ላይ የሚጻፉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በአግባቡ በመሰነድ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ያሳሰቡት ተሳታፊዎቹ በዞኑ ምክር ቤት በተወሰነው ውሳኔ መሠረት በየደረጃው ባለው የዞኑ መዋቅር ቋንቋውን በመደበኛ የመንግሥት ሥራ ላይ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከካፋ ቱባ ባህላዊ ዕሴትና ተውፊቶች አንዱ የሆነውንና በብሔሩ ዘንድ በአደባባይ በድምቀት የሚከበረውን የአዲስ ዘመን መለወጫ (ማሽቃሮ) በዓል ህዝባዊ መሠረትን በማጽናት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማይዳሰስ ቅርስነት ማስመዝገብ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

በጊዜ ሂዴት የተረሱ ባህላዊ ክዋኔዎች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ የብሔረሰቡን ታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች በማልማት በተገቢው መጠቀም እንደሚገባም በድረኩ ተነስቷል።

ባለፉት 30 ዓመታት የካፊ ኖኖ ቋንቋን በማሳደግ የዞኑ የሥራናየትምህርት ቋንቋ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን የገለጹት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በዚህም በስርዓተ ትምህርት ከ1 ክፍል ጀምሮ በዩኒቨርስቲ ደረጃ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀግብር እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

የዞኑ መንግሥት ባህልና ቋንቋውን ለማሳደግ የተጀማመሩ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ እንዳሻው የአከባቢው ተወላጅ ምሁራን በብሔሩ ታሪክና ባህል ላይ የሚሰሩትን የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ባህሉን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ሚና መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊና የዲጂታል ሚዲያ አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ዶ/ር መስፍን ወዳጆ በተላይም የባህል ምግቦችን በሆቴል ለተጠቃሚዎች ማቅረብ እንደሚገባ አስታዉቀዋል።

የባህል ምክር ቤት ስብሰባ አቶ ብረሀኑ ሀይሌ በበኩላቸው የዞኑ መንግሥት የካፋ ባህልና ታሪክ ለማልማት እያደረገ ያለው ተግባር አበረታች መሆኑን በመግለጽ ወጣቱ ትውልድ ለባህሉ ዕድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *