የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ የማዕድን ሃብቷን ለእመርታዊ ለውጥና የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታውል እያደረገ ነው

Spread the love

የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ የማዕድን ሃብቷን ለእመርታዊ ለውጥና የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታውል እያደረገ ነው ሲሉ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጹ።

ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በመደመር እሳቤ የማዕድን ሀብትን በማልማት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያስመዘግብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕድን ዘርፉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው አምስት ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለግብርና፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኮንስትራክሽንና ለሌሎች ዘርፎች ግብዓት የሚሆኑ እምቅ የማዕድን ሀብቶች ባለቤት መሆኗንም ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት ያለውን ሀብት የመለየትና ከሀገራዊ ፖሊሲ ጋር የማስማማት ስራ በመስራቱ በዘርፉ ያለው ኢንቨስትመንት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲያድግ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዘርፉ የተከናወነው ስር ነቀል የእይታ ለውጥ በዋናነት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ማስቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ከዘርፉ ሦስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቁመው፤ በተያዘው ዓመትም ከዚህ በእጅጉ የላቀ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት በዘርፉ ያደረገው የእይታ ለውጥ ከገቢ ምንጭነት ባለፈ ለፋብሪካዎችና ግንባታዎች የሚፈለጉ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ አምርቶ መጠቀም ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ይህም ሀገሪቱ የነበረባትን የውጭ ጥገኝነት በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

የማዕድን ምርትን በሀገር ውስጥ በስፋት መጠቀም ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በፖሊሲው አማካኝነት ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የማዕድን ዘርፉ ለተለያዩ ዘርፎች ያለውን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባትም በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *