የበጋ መስኖ ስንዴ “ባህላቸው” የሆነባት የአሩሲ አንገላ ሞዴል መንደር ስኬት

Spread the love

ከአንድ ማሳ በዓመት ሶስቴ ምርት፤ በሄክታር እስከ 39 ኩንታል እየተገኘ ነው

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በዳውሮ ዞን ኢሠራ ወረዳ ተዓምር እየሰራ ነው። በተለይም የአሩሲ አንገላ ቀበሌ አርሶ አደሮች ልማቱን ከሙከራነት አልፈው የዓመት ሥራ “ባህላቸው” በማድረግና ወቅቱን በጉጉት በመጠበቅ ለሌሎች ተምሳሌት ሆነዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሠለሞን ተክሌ እንደገለጹት፣ በ2014 ዓ.ም በ495 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው ይህ ንቅናቄ፣ ዛሬ ላይ 164 ምንጮችን በመጠቀም በ26 ቀበሌዎችና 68 ክላስተሮች ውስጥ ወደ 1,249 ሄክታር በማደግ ወረዳውን የስኬት ማሳያ አድርጎታል።

የአሩሲ አንገላን ስኬት ወደ አጎራባች ቀበሌዎች በተሞክሮ እያሰፋፋን ነው ያሉት አስተዳዳሪው፣ የመስኖ አውታሮችን ብቻ ሳንጠብቅ ወንዞችን፣ ምንጮችንና የውሃ ፓምፖችን በመጠቀም የተፈጥሮ ሀብታችንን ለልማት እያዋልን ነው ሲሉ የወረዳውን የፈጠራ አቀራረብ አስረድተዋል። አቶ ሠለሞን ይህ ሀሳብ ወደ ሀብት የተቀየረበት ትልቅ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሌሎችም ይህን ተሞክሮ በመከተል የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ለኤክስፖርት እንዲበቃ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ስኬት ዋነኛ ማሳያ በሆነችው የአሩሲ አንገላ ቀበሌ፣ በ3 ክላስተሮች 289 ሄክታር መሬት በበጋ ስንዴ መሸፈኑን የቀበሌው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሠለ ደባንቾ ገልጸዋል። በመጀመሪያ የአርሶ አደሩን ግንዛቤና አስተሳሰብ ለመለወጥ ብዙ ሰርተናል፤ አሁን ግን ከሚያገኙት ጥቅም አንጻር ፍላጎታቸው እጅግ ጨምሯል ሲሉ የለውጡን ሂደት አስታውሰዋል።

የአርሶ አደሮቹ ተጨባጭ ምስክርነት

የዚህ ለውጥ ህያው ምስክር የሆኑት ሞዴል አርሶ አደር ወ/ሮ ካሰች ታዬ ናቸው። የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ከጀመርኩ አራት ዓመት ሆኖኛል” የሚሉት ወ/ሮ ካሰች፣ ባላቸው 8.5 ሄክታር መሬት ላይበዓመት ሶስቴ በማምረት ህይወታቸው እንደተለወጠ ይናገራሉ። “በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ፓኬጅና በባለሙያዎች ድጋፍ ከአንድ ሄክታር እስከ 39 ኩንታል ምርት እናገኛለን በማለት የስኬታቸውን ምስጢር አጋርተዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር አቶ በራታ ቴማ በበኩላቸው፣ በክላስተር በመደራጀት በፈረቃ ውሃ ማጠጣታቸውና የአረም ቁጥጥርን በጋራ መስራታቸው ለስኬታቸው ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል። ከራሳችን ፍጆታ አልፈን ለገበያ እያቀረብን ነው፤ ሌሎችም ያላቸውን የውሃ አማራጭ ተጠቅመው ቢያለሙ በእጅጉ ይጠቀማሉ ሲሉ ልምዳቸውን አካፍለዋል።

የአሩሲ አንገላ ተሞክሮ፣ ጠንካራ የመንግስት ራዕይ ከአርሶ አደሩ ቁርጠኝነትና የፈጠራ አሰራር ጋር ሲጣመር እንዴት ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ደማቅ ምሳሌ ሆኗል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *