




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ የምግብና ስርዓተ- ምግብ ደህንነት ማሻሻያ /BREFONS/ፕሮጀክት እና የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክቶች/DRIVE/ የ2018 በጀት ዓመት የስቲሪንግ ኮሚቴ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይት መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ፕሮጀክቶቹ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ዕውን ለማድረግ ዓይነተኛ ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም የአርብቶና ከፍል አርብቶ አደሮች የተሻለ የአመራረት ዘይቤን በመከተል ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ የአመራረት ዘዴ በመውጣት ለገበያ እንዲያመርቱ በማስቻል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የገጠር ትራንፎርሜሽንን ዕውን ለማድረግ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት መሠረተ ልማትን በመዘርጋት፣የእንስሳት ዕሴት ሰንሰለትን በመጠበቅ ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ በመስራት፤ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ማስረሻ ተናግረዋል።
ለገጠር ትራንስፎርሜሽን የሀብት ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ያሉ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለውጤታማነቱ የስትሪንግ ኮሚቴ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መቱ አኮ የመድረኩ ዓላማ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም በፕሮጀክቱ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን በጋራ ለማረም እንደሆነ አንስተዋል።
በቢሮ ደረጃ የተገመገመ ሪፖርትና ከፌደራል የተሰጠውን ግብረ መልስ መነሻ በማድረግ ጥልቅ ውይይት በማድረግ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን እንዲከፋፈሉ አሳስበዋል።
በውይይቱ የሁለቱ ፕሮጀክቶች የ2017,ዓ/ም / ሪፖርት በፕሮጀክቱ አስተባባሪ በሆኑት በአቶ ተስፉዬ ኦይጌሌች ለተሳታፊዎች ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
በሪፖርቱ ላይ የምግብና ስርዓተ- ምግብ ደህንነት ማሻሻያ /BREFONS/ ፕሮጀክት 6372 የማህበረሰብ ክፍልን ተጠቃሚ የሚያደርግ 15 አነስተኛ የውሃ ምንጭ ግንባታ መጠናቀቁን እና 41 አነስተኛ የውሃ ተቋማት የጥናትና ዲዛይን ስራ መጠናቀቁን ተገልጿል።
የእንስሳት ጤናን ከማሻሻል በጎባ ወረዳ እየተገነባ ያለው የእንስሳት ጤና ክሊንክ ግንባታ 85%፣ የማጂ የእንስሳት ጤና ኬላ 88% እንዲሁም የጎሪነስ ጤና ኬላ 88% ላይ መድረሱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
በስራ ዕድል ፈጠራ በዶሮና እርባታ፣ በፍየል ማሞከት፣ በንብ ማነብ እንዲሁም በሙዝና አትክልት ልማት በ17 ቡድን በማደራጀት 347 ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ በሪፖርቱ ተብራርቷል።
የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክቶች/DRIVE/፦ ዘርፉ ለአየር ንብረት ለውጥ የአርብቶ አደሮችን አቅም በመገንባት ጥቅል የተቀናጀ የፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ዓላማ አደርጎ የሚሰራ፤ በእንስሳት ዕሴት ሰንሰለት ውስጥ ለግሉ ኢንቨስትመንትና ለአርብቶ አደሩን የሚደገፍ ነው።
በተሰራው ስራና ግንዛቤ 1500 አርብቶ አደሮች የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ታቅዶ 1299 አርብቶ አደሮች 30% ቅድሜ ኢንሹራንስ ክፍያ ብር 2,834,574 ተሰብስቦ ወደ ኢንሹራንስ ተቋም ገቢ በማድረግ በዚህም ለ4,465 እንስሳት ኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ በፕሮጀክቱ እስካሁን የተሰሩ ተግባራት ውጤት የታየበት መሆኑን በማንሳት፤ ከመንግስት የሚመደበው ማቺንግ ፌንድ፣ የስትሪንግ ከሚቴ በተቀመጠ ጊዜ ከመወያየት፣ ከኮንትራክተሮች አቅም ውስንነት ጋር በግንባታ መዘገየትና መቋረጥ ጉዳዮች በቀጣይ በትኩረትና በቅንጅት መሰራት እንደሚገባ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።
በመጨረሻም በውይይቱ ለተነሱ ጥያቄዎች በሚመለከተው አካላት ምላሽ የተሰጠ ሲሆን በ2018 ዓ/ም ዕቅድ ላይ ስትሪንግ ኮሚቴው ውይይት በማድረግ በ2017 ዓ/ም የተመዘገበውን በማጠናከር ጉድለቱን ትምህርት በመውሰድ በማረም ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በጌታሁን ግርማ
