




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ማጠቃለያ ከብረ በዓል በሚዛን አማን ከተማ ተከበረ።
የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መብት መከበር ዋስትና የሆነው የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የፀደቀበት በህዳር 29 ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ኩነቶች እየተከበረ መቆየቱም ተጠቁሟል።
በዛሬው ዕለት የክልሉ ብሔረሰቦች ምክርቤት 20ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል ከክልሉ ከተውጣጡ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በሚዛን አማን ከተማ አደባባይ በድምቀት አክብረው ውለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አፍቅሬ አማን በበዓሉ መዝጊያ ባደረጉት ንግግር፣ ሀገራችን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ባህል ብዘሃነት የምገኝባት ሀገር በመሆኑ ብዝሃነትን በማስተናገድ ሀገራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ረገድ የበዓሉ መከበር የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው ብለዋል።
የዘንድሮ በዓል ለየት የሚያደርገው የለውጡ መንግስት የሀገርን ጠቅም ለማስጠበቅ እየተጋ ያለበት፣ለሀገራችን ተስፋ የሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች የተጀመሩበት፣ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የተጠናቀቀበት፣እንዲሁም ከፋፋይ እና ነጣጣይ ትርክቶችን በመፋቅ የሀገር መንግስት ግንባታ ሂደት የተጀመረበት ወቅት መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
የሀገራችን ሀገመንግስት ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተለየ እውቅና የሰጠ በመሆኑ በሀገራችን የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን ወጋቸውን እያለሙ እንዲጠቀሙ እንዲያለሙና በሀገር ልማትና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ተልቅ እድል የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬ የምናከብረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የዚህ ውጤት ማሳያ ሲሆን ሀገራችን የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ዲሞክራሲን በማስፋትና ችግሮቻችን በመነጋገርና በመወያየት መፍታት ባህል እንዲሆን እየተጋች በምትገኝበት ወቅት ላይ መሆኑን አቶ ፍቅሬ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ጌታቸው ኬኒ፣የብሔረሰቦች ቀን በዓል በህዝቦች መካከል መተዋወቅ፣መቀራረብ፣ትስስርና አንድነት የሚጠናከርበት ፣የብሔር ብሔረሰቦች ቱባ ባህሎች ከዕሴቶቻቸው ጋር የሚያድግበት ትልቅ የኢትዮጵያ ህዝቦች በዓል እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ያላት ሀገር እንደመሆኗ በህዝቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶች ሲኖሩ ችግሮችን የሚፈቱበት የዳበረ ልምድ እንዳለት ጠቅሰው ግጭቶች ቢፈጠሩ እንኳ በሰለጠነ መንገድ እንዲፈታ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም አስረድተዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አቶ ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፣በዓሉ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችል ህገ-መንግስት የጸደቀበት ቀን በመሆኑ ህብረብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ እየተከበረ መቆየቱን ተናግረዋል።
የበዓሉ መከበር የተጀመረውን ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ እውን ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውና በክልል ደረጃ በሚገኙ መመዋቅሮ ብሔር ብሔሮችና ህዝቦችን ባሳተፈ መልኩ መከበሩን በመግለፅ ለዚህ ዓላማ መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱት አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ብዝሃነትን በማስተናገድም ሆነ አገራዊ አንድነትን በማረገገጥ እና ሕብረ ብሔራዊነት በመገንባት ረገድ የበዓሉ መከበር የከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙት አፈጉባኤው የበዓሉ መከበር ብሔር ብሐረሰቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ ህብረ ብሐራዊ አንድነት እንዲጠናከርና እንድዲጎለብት እንዲሁም ታሪክና እሴቶች እንዲጎለብቱ የሚያግዝ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ዕለቱን መክበር በአብሮነትና እኩልነት ላይ ግንዛቤን በመፍጠር የተጀመሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራትን ለማስቀጠል ይረዳል ያሉት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን ናቸው።
የክልሉ እና ዞን ከፍተኛ አመራርና ባለሙያዎች ፣ተማሪዎች እና መምህራኖች ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የቀበሌ አስተዳደሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦችም ተሳታፊ ሆነዋል።
በካሳሁን አሰፋ
