ቋሚ የሥራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል ትኩረት መስጠት ይገባል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
Spread the love
ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢንጂነር)

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ አፈጻጸምን ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።

ቢሮው በሩብ ዓመቱ በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ስራ ላይ በተሰሩ ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ገምግሟል።

በክልሉ ስራ ፈላጊ ዜጎችን በየማህበራዊ መሠረት በመለየት የክህሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ በመድረኩ ተብራርቷል።

በዚህም ከተለዩ ከ101 ሺህ 792 ሥራ ፈላጊ ዜጎች ውስጥ በሩብ ዓመቱ ወደ 8 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠር መቻሉ ነው የተገለጸው።

የክልሉ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በበጀት ዓመቱ 4 ሚሊዮን ብር የመደብ ሲሆን ከዞኖች፣ከወረዳዎች እና ከሌሎች ምንጮች የተገኘ ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በሩብ ዓመቱ ለ7 አነስተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከ15 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ የካፒታል ዕቃዎችን ማቅረብ መቻሉም በመድረኩ ተገልጿል።

ለወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል በመፈጠር የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለማሻሻል የተጀመረውን ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻዎች ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

ነባር ኢንተርፕራይዞችን ደግፎ በማሸጋገር ለአዳዲሶቹ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በተቀመጠለት ጊዜ መመለስ እንዳለበት ተናግረዋል።

የካፒታል ዕቃዎችን ለሚወስዱ አነስተኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የመስሪያና መሸጫ ቦታዎች ማመቻቸት እንደሚገባ የተገለጸ ሲሆን ከኦሞ ባንክ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የብድር አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ለስራ ዕድል ፈጠራ በታችኞቹ መዋቅሮች የሀብት አመዳደብ ላይ መሻሻል እንዳለ ያነሱት የቢሮው ኃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ ልየታው ባለድርሻዎችን በማሳተፍ በንቅናቄ እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለው በካፋ ዞን በሰፈራ ፕሮግራም እንዲሁም በዳውሮ ዞን በመካናይዜሽን ለወጣቶች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ለሌሎች ተሞክሮ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የሁለተኛው ዙር የስራ ፈላጊዎች ለየታ በትኩረት እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን ቋሚ ሥራ ዕድል ፈጠራን ማዕከል በማድረግ ለወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አበዳሪ ተቋማት አከባቢ የሚስተዋለው ማነቆ ከተፈታና የእርሻ ማሽነሪዎች ጥገና ጉዳይ መፍትሔ የሚሰጠው ከሆነ የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልል እና የዞን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *