የግብርና ፍኖተ ካርታ በግብርናው ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን የሚፈታ ነው።

Spread the love

ግብርና የህብረተሰቡ ኑሮ መሠረትና የኢኮኖሚ ዘርፍ ትልቅ አቅም ነው ::

ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር እና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ትብብር የተዘጋጀ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት የግብርና ፍኖተ ካርታ ጥናት ሰነድ ርክክብ ተደርጓል ።

በጥናት ሰነዱ ርክክብ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ግብርና የኢኮኖሚው ዘርፍ ትልቅ አቅምና የህብረተሰቡ የኑሮ መሠረት እንደሆነ ተናግረዋል ።

ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የተዘጋጀው የግብርና ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ሲገባ የአርሶአደሩን እና የአርብቶአደሩን ህይወት የሚቀይርና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የግብርና ፍኖተ ካርታ በእርሻ ስራ፣በእንስሳት ፣በምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲሁም ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሂደት በተጨባጭ የሚደግፍ መሆኑንም ተናግረዋል ።

ግብርናን ለማዘመን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ፣የምርጥ ዘር አቅርቦት ፍላጎት ፣የግብርና ስራዎች ውጤት የገበያ ትስስርና መለስተኛ ኢንዱስትሪዎች በክልሉ እንዲፈጠሩ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የተዘጋጀው የግብርና ፍኖተ ካርታ የመልማት አቅምን ለማሳደግና በግብርና ስራዎች ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

ኢንስቲትዩቱ በክልሉ በ11ወረዳዎች ከ170 በላይ ቀበሌዎች በተመረጡ የሰብል ልማት ከምርት እስከ ግብይት ድጋፍ በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።

በዕለቱም በነበረው መድረክ የግብርና ፍኖተ ካርታ ጥናት ሰነድ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የጥናት ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ።

በዕለቱም ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ምትኩ፣አቶ መስፍን ጉብላእና ዶክተር ጴጥሮስ ወ/ጊዮርጊስ በሰጡት አስተያየት የግብርና ፍኖተ ካርታ በክልሉ የተጀመረውን የግብርና ስራዎች ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል ።

በክልሉ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ውጤታ ለማድረግ የልምድ ልውውጥና ተሞክሮ ቀምሮ በመውሰድ መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል ።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ ለሚከፈተው የሳተላይት ቢሮ ተባብሮ ለመስራት የውስጥ ቁሳቁስ እንደሚያሟላ ዶክተር ጴጥሮስ ወ/ጊዮርጊስ ቃል ገብተዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ የዞን አስተዳዳሪዎች የግብርና ፍኖተ ካርታ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ።

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንደፍሮ ንጉሴ የግብርና ፍኖተ ካርታ አርሶ አደሩ በኩታ ገጠም ተደራጅተው ከራስ አልፎ ለገበያ የሚያቀርቡበትን ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በዘርፉ በሚሰሩ ስራዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የአርሶ/አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ማንደፍሮ በክልሉ ሳተላይት ቢሮ በመክፈት እንደሚሰራም ተናግረዋል ።

ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እዉን መሆን ደግሞ የባለድርሻ አካላት ሚናና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።

በቀረቡት የጥናት ሰነዶች በተሳታፊዎች አሰተያየት እና ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *