


በክልሉ በአርሶአደር እና በባለሀብቶች እንዲሁም በተለያዩ አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የተሻለ ምርት ለማምረት እየተሰራ እንደሆነ ታዉቋል።
በ2016 በጀት ዓመት በ11 ሺህ ሄክታር መሬት የበጋ ስንዴ ለማምረት እቅድ ተይዞ የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በዞኖች የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ የማሳ ልየታና የዝግጅት ስራዎች መጀመሩ ተገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት የግብርና ልማት ሠራተኞች የትኩረት ማዕከል ማሳ ላይ እንዲያደርጉ በማድረግ ያሉ የውሃ አማራጮችንና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጭምር በመጠቀም የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዉም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና መካናይዜሽን ተግባራዊ በማድረግ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የግብርና ስራን ለወጣቶች አንዱ የሥራ ዕድል መፈጠሪያ በማድረግ የ ለዚህ ዓላማ የመደበውን የእርሻ ማሽኖችን መጠቀም ለምርትና ምርታማነት መትጋት እንደሚገባ ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስበዋል።
በዶሮ ጫጩትና የወተት ላም እርባታ የታየው መነቃቃት በሌሎችም የሌማት ትሩፋት ስራዎች ላይም መጠናከር እንዳለበት የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበጋ የመስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ለማግኘት ከአከባቢው ስነምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነ የዘር አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተጣለውን ግቢ ለማሳካት የአመራርና ባለሙያዎች ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የውሀ አማራጮችን ለእርሻ ሥራ ዋና ግብዓት አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ የተገነቡ የመስኖ ተቋማትን በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ሂዴት ማስገባት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነትና ጠባቂነት ተላቆ በአመት ሶስት ጊዜ በማምረት የምግብ ዋስትናዉን እንዲያረጋግጥ ማስቻል አለብን ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከዘር አቅርቦትና መስኖ አውታሮች ዙሪያ ልገጥም ይችላል ያሉትን ጥያቄ አንስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
የንቅናቄ መድረኩ እስከቀበሌ በተጠናከረ መልኩ ይደረጋልም ተብሏል።



በዕድገቱ በዛብህ
