



የሺሾ እንዴ ወረዳ እንተርፕራይዝ፣ንግድ፣ገበያ ልማትና ስራ ክህሎት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሳዬ አበቶ እንዳሉት በወረዳው ወጣቶች በሰፈራ ማስገባት የጀመረው በ2013 ዓ ም ክረምት አከባቢ እንደነበር ገልጸው ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በሰፈራው ፕሮግራም የወጣቶችን ለማስገባት ከአመለካከት ጀምሮ በርካታ ፈተናዎችን የተሻገረ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አሳዬ በተሰራው ጠንካራ ስራ ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶችን ህይወት መቀየር እንደተቻለ ገልጸዋል።
ወጣቶቹ በ5 ቀበሌዎች መደራጀታቸውን የገለፁት ኃላፊው በሁሉም ቀበሌዎች ሁሉም የግብርና ምርቶች እንደምመረቱ ጠቁመዋል።
ለአከባቢው ተስማም የሆኑ ምርቶች ማለትም ሙዝ፣ አቮካዶና ፓፓያ ምርቶች በስፋት እንደምመረቱ በተጨማሪ ቦለቄ፣ ማሾ፣ኦቾሎን ፣ነጭ ጤፍና ነጭ ማሽላና መሰል ምርቶችን ወጣቶች በማምረት ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነም ተናግረዋል።
የአከባቢውን አየር ሁኔታ ሙቀታማ በመሆኑ የፍየል ማሞከት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አሳዬ አንድ ወጣት በአማካይ ከ40 እስከ 50 የፍየል ሙክት ስራ በትኩረት እየሰሩ ነው ብለዋል።
የወጣቶችን ህይወት ከመቀየር ባለፈ የአከባቢውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል።
የወረዳው መንግስት ለወጣቶች ሰፈራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ እንደሆነ የሺሾ እንዴ ወረዳ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ጌታቸው ተናግረዋል።
በወጣቶች የሚመረቱ የግብርና ምርቶች በአግባቡ ወደ ገበያ ለማቅረብ መሠረተ ልማት ወሳኝ በመሆኑ ከጨሎ እስከ ጎራ ፉል ውሃ 24 ኪሎ ሜትር መንገድ በወረዳው መንግስት ድጋፍ የከፈታ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
የጤና አገልግሎትን ለመስጠት የጤና ኤክስቴንሽን ተመድበው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልፀው የጤና ተቋማት የመገንባት ስራ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል።
በርካታ ህፃናት በቀበሌዎች መኖሩን ያረጋገጡት አቶ አስራት እነኝህ ህፃናትን ዳስ በማሰራት የማስተማር ተግባር የተጀመረ ብሆንም ትምህርት ቤቶችን መገንባት የጋራ ጥረት እንደሆነም ገልጿል።
የክልሉ መንግስት ቦታውን በጎበኘበት ወቅት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ቃል መግባቱን ያብራሩት አቶ አስራት በተገባው ቃል መሰረት መሰረተ ልማቶችን በመጠገንና በመዘርጋት አጋርነታቸውን ልያሳይ ይገባል ማለታቸዉን የሺሾ እንዴ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዘግቧል።
