የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተግዳሮት በምግብ እህል ማምረት ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት የሣይለም ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ገለጸ ።

Spread the love

እንደ ጽህፈት ቤቱ ገለጻ ከሆነ ችግሩ የተፈጠረው የወረዳው አርሶ አደሮች ከእርሻ ሥራ ይልቅ ለከብት ድለባና እንስሳት እርባታ ከፍተኛውን ትኩረት የሚሰጡ በመሆናቸው ነው ።

የጽ/ቤቱ ዋና ኃላፊ አቶ ማሞ መንገሻ እንዳብራሩት :- በዘንድሮ መኸር እርሻ 6 ሺ 9 መቶ 50 ሄክታር ለማረስ ታቅዶ 5 ሺ 912 ሄክታር በላይ ታርሷል ። በዚህ የመኸር እርሻ ሥራ ላይ 5 ሺ 766 አ/አደሮች ተሳትፈዋል ።

በዘር ከተሸፈነው መሬት ስንዴ 561 ሄ/ር በላይ ፣ ገብስ 1 ሺ 67 ሄክታር በላይ ፣ ጤፍ 1 ሺ 347 ሄ/ር በላይ እንዲሁም አተር 1 ሺ 326 ሄክታር በላይ ይገኝበታል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ተልባና አጃን የመሳሰሉ ምርቶችም በመኸር እርሻው ተካተዋል ።

በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ሠፊ ክፍተት መኖሩን ያመላከቱት የወረዳው ግብርና አካባቢ ጥበቃና ሕብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ማሞ መንገሻ በዘር ከተሸፈነው 5 ሺ 912 ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ 36 ሄክታር ስንዴ እና 8.25 ሄክታር ገብስ ብቻ በቴክኖሎጂ ከመዘራቱ ውጪ ሌሎቹ በተለምዶአዊው መንገድ ነው የተዘሩት ብለዋል ።

በቴክኖሎጂ አጠቃቀም በኩል ለተስተዋለው ተግዳሮት በምክንያትነት የተገለጸው የግብዓት ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረው አንጻር እጅግ ከፍ ብሏል ፤ እንዲሁም በመደበኛ ከሚለማውና በቴክኖሎጂ መካከል ብዙም የተራራቀ የምርታማነት ልዩነት የለም የሚል የተዛባ አመለካከት በአርሶአደሩ ዘንድ መስተዋሉ እንደሆነ ተጠቅሷል ።

በተለይም አብዛኞቹ የወረዳው አርሶ አደሮች ከእርሻ ሥራ ይልቅ ለከብት ድለባና እንስሳት እርባታ ከፍተኛውን ሥፍራ የሚሰጡ መሆኑም ሌላኛው ምክንያት እንደሆነም ኃላፊው አመልክተዋል ።

እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ አርሶ አደሩ ሁለቱንም ተግባራት አጣምሮ በውጤታማነት እንዲተገብር እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች የተገኙ አጋጣሚዎችን ጭምር በመጠቀም የተስተዋለውን የግንዛቤ እጥረት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።

ከዚህ ውጪም የተስተዋለውን ክፍተት ለማረም በወረዳው ምክር ቤት አ/አደሩ በምግብ እህል ራስን ከመቻል አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከቴክኖሎጂ ውጭ መሆን እንደሌለበት የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ እና በመኸር ወቅት ያጣነውን በመስኖ ለማካካስ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዋል ።

ያምሆኖ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታይ መሻሻሎች አሉ ያሉት የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ማሞ መንገሻ በጥቂት አርሶ አደሮች ዘንድም ቢሆን የታየውን መሻሻል ለማስፋት ጽ/ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ይሰራል ብለዋል ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ከመኸር እርሻው 30 ሺ ኩንታል ምርት ከዋና ዋና ሠብሎች ይጠበቃል ።

ይህም አምና ከነበረው ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 10 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አስረድተዋል ።

ዘገባው የወረዳው የሣይለም ወረዳ የመን/ኮ/ጉ/ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *