ዘመኑን የዋጀው ዲጂታል አገልግሎት

Spread the love

በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ አቅማቸውን በማጎልበት ዲጂታል አሰራርን ተግባራዊ እያደረጉ ይገኛል።

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማትም ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆኑ የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ የበርካቶች ጊዜና ጉልበት መቆጠብ ችለዋል።

በጉዳዩ ላይ የኢኖቬሽንናቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) እና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፈጠነች መስቀሌ ከኢቢሲ አዲስ ቀን የሀገር ጉዳይ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ባላፉት አምስት ዓመታት 43 የፌዴራል ተቋማትና የከተማ አስተዳዳሮች አገልግሎታቸውን ዲጂታላይዝድ ማድረጋቸውን የገለፁት ዶ/ር ይሽሩን፤ ሌሎች ተቋማትም ይህንን ዓርአያ እንዲከተሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

መንግስት በአምስት ዓመታት ውስጥ 2500 አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተው፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዋናነት ዕቅዱን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎታቸውን ዲጂታላይዝድ ያደረጉ ተቋማት ጥሩ አፈፃፃም እንዳላቸውም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት እንዲሁም የጉሙሩክ ኮሚሽንን የመሳሰሉ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ በማድረግ ጥሩ አፈፃፀም ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ተቋማት ዘመናዊውን አገልግሎት ያለመረዳት፣ ተጠቃሚዎችም ወደ ዲጂታል አገልግሎት ለመምጣት መቸገር፣ የመሰረተ ልማት ችግሮች፣ የዲጂታል ክህሎት እጥረትና በተቋማት መካካል የሲስተም ትስስር አለመኖር አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ እንዳይሆኑ ተግዳሮት እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡

ችግሮቹን ለመቅረፍ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል አስተዳደር ስትራቴጂና ሰነድ በማዘጋጀት አገልግሎቶች በአስገዳጅነት ወደ ዲጂታል ስርዓት እንዲገቡ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም አገልግሎት ሰጪውና ተገልጋዩ ግንዛቤ እንዲያገኙ የተለያዩ ስልጠናዎችን እየተሰጡ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡

ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍም ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ተደራሽነት ለማሳደግና ከዳታ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመፍታት የዳታ ማከማቻ ማዕከላት የማስፋፋት ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

መምህርና ተመራማሪ ፈጠነች መስቀሌ በበኩላቸው ተቋማት አገልግሎት አሰጣታቸውን ዲጂታላይዝድ ማድረጋቸው ግልፀኝነትና ተጠያቂነት እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል።

“አገልግሎትን ለማዘመንና ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እራስን ከቴክኖሎጂ ጋር ማላመድ ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ አብዛኛው ጊዜ የሚነሳው ትልቁ ጥየቄ የመረጃ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን ያነሱት መመህሯ፤ የመረጃ ደህንነትና የሳይበር ጥቃት መከላከል አቅም ለማሳደግ ተቋማት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *