


የኢሠራ ተራራ በዳዉሮ ዞን፣ኢሠራ ወረዳ በአሩስ አንገላና አሩስ ባላ ቀበሌ መካከል የሚገኝ ትልቁ ተራራ ስሆን የተራራ ስያሜ፥ ኢ-ሣራ (እሱ ሠላም) ከሚለው መጠሪያ ኢሠራ ተብሎ እንደተጠራ የአከባቢው የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።
እንደ ታሪክ አዋቂዎች ገለጻ፥ በቀድሞው
ጊዜ ከወጪ ውረራ ለማምለጥ አቅም ያላቸው ታዋቅ ሰዎች በተራራው ባለው ዋሻ ከተሸሸጉ በኃላ የአከባቢው ሰዎች ስንቅ ለማቃበል የሄደውን ሰው ስለ እነዛ ሰዎች ደህነነት ስጠይቁ “ኢ-ሣራ” (እሱ ሠላም ነው) ማለትም እሱ ሠላም ነው ከሚለው መነሻ ተራራው ስያሜውን እንዳገኘ ይገልጻሉ።
ተራራው ከባህር ጠለል በግምት 2ሺህ 800 ሜትር ላይ የሚገኝ ሲሆን አጠቃላይ የሚይዘው የመሬት ስፋት ከ151.2 ሄ/ር በላይ መኾኑን ከወረዳው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማር ተራራውን በከበበው ለምለም ጫካ ውስጥ የተለያዩ ለመድኃኒትነት ጠቀሜታ ያላቸው እጽዋትና የከርስ ምድር ውሃ እንዳለ ይነገራል።
ተራራው ከቀደምት ጊዜ ጀምሮ ባለው ይዘት
በአከባቢው ማኅበረሰብ ተጠብቀው የሚገኝ ሲኾን በተራራው ጫፍ ኾነው ሩቅ ያለውን አጎራባች ወረዳዎች፣ የኮንታ ዞን አማያ ከተማን እንዲሁም ሌሎች አካባቢዎችን ማየት ይቻላል።
ከተራራው ግርጌ የሚወጡ ከርስ ምድር ውኃ ምንጮች እጅግ በጣም ንፁህ በመኾኑ የአከባቢው ስዎች ሳይቸገሩ ለራሳቸውና ለቤት እንስሳት ያጠጣሉ።
ይህንን አስደናቂ ተራራን የአከባቢው ሰዎች ለማስተዋወቅ ስባል የወረዳው ስም በተራራው ስም ኢሠራ ወረዳ ተብሎ መሰየሙም ተገልጿል።
በዕድገቱ በዛብህ
