የቲካሻ በንጊ በዓል አብሮነትንና የወንድማማችነት እሴቶች የሚገለጽበት ድንቅ በዓል ነው፦አቶ አለማየሁ አለሙ

Spread the love

የሸኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል የሆነው “ቲካሻ ቤንጊ” በሸካ ዞን በቴፒ ማዕከል በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ እየተከበረ ነው።

በዓሉ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የብልፅግና ዓመት እንዲሆን በባህላዊ አባቶች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን፣ የብሔረሰቦችን ማንነት የሚገልጹ የተለያዩ ባህላዊ ጭፈራዎችና ዜማዎች ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል።

የቲካሻ በንጊ በዓል አብሮነትንና የወንድማማችነት እሴቶች የሚገለጽበት ድንቅ የብሄረሰቡ በዓል ሲሉ የሸካ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙ ተናገሩ።

ባህል የአንድ ማህበረሰብ ቋንቋ፣ እሴትና ማንነት ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም ለሀገር መንግስት ግንባታ ጉልህ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።

የ“ቲካሻ ቤንጊ” የአብሮነትና የመተሳሰብ ነባር እሴቶች በምርምርና በጥናት ተደግፈው ለኢኮኖሚ ምንጭ እንዲውሉና ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ አስፈላጊ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ መልኩ የየኪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ተሰማ፣ “ቲካሻ ቤንጊ” የሸኮ ብሔር ለፈጣሪው ያለውን ጥልቅ ክብርና ምስጋና የሚገልጽበት እንዲሁም ተፈጥሮና ሰው ዳግም የሚታደሱበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

የቴፒ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገላቲያስ በበኩላቸው፣ ይህ በዓል የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመቻቻልና የፍቅር እሴቶችን የሚያጎላ እንዲሁም የብሔርና የብሔረሰቦች ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናከር ድንቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የሸኮ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የባህልና የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *